የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ያለ ልዩነት ለኢትዮጵያ ሕልውና በጋራ በቆምንበት ወቅት መከበሩ ልዩ ትርጉም አለው

102

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) "የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን የምናከብረው ያለ ልዩነት ለኢትዮጵያ ሕልውና በጋራ በቆምንበት ወቅት መሆኑ ልዩ ትርጉም አለው" ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

16ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ወንድማማችነት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ በድሬዳዋ ይከበራል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የኢትዮጵያዊያን ዋነኛ መገለጫ በብዝሃ-ማንነት የተጋመደ ጠንካራ አንድነት መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን አሸባሪው ህወሓት ይህንን ሃቅ የካደ ሴራ ሲያከናውን መቆየቱን ነው ያብራሩት፡፡

የሽብር ቡድኑ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አካል በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የክህደት ጥቃት በመፈጸም ለኢትዮጵያዊያን ያለውን ጥላቻ በግልጽ ማሳየቱን አስታውሰዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በስልጣን በቆየባቸው ጊዜያት የኢትዮጵያዊያንን ሕብረ-ብሔራዊነት እንደ ጸጋ ከመቁጠር ይልቅ የልዩነት ምንጭ ብቻ አድርጎ በመጠቀም እርስ በእርስ ለማባላት ሲሰራ መቆየቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ይህ ቡድን ኢትዮጵያዊያንን በማንነት ከፋፍሎ ለማባላት ያደረገው ሙከራ አልሳካለት ሲለው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለመ ግልጽ ወረራ መፈጸሙን አፈ-ጉባኤው ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያለ ልዩነት አንድ ሆነው በመቆም አሸባሪውን የህወሓት ወራሪና ተላላኪዎቹን እየመከቱ እንደሚገኙ አውስተዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያዊያን በደም የተሳሰረ አንድነት እንዳላቸው በተግባር ማሳየታቸውን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ 16ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ልዩ ትርጉም እንዳለው አብራርተዋል፡፡

በዓሉም ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ቃል የሚገቡበት እንደሚሆንም ነው የተናገሩት፡፡

በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን ጠብቀው የኢትዮጵያን እውነት በማሳወቅ ረገድ  ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ መሆኑንም አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገልጸዋል፡፡

በዚህም "ኢትዮጵያዊነት በቦታ የማይገደብ አገር የመውደድ ምልክት መሆኑን ለዓለም ሕዝብ በተግባር አሳይተዋል፤ እኛ ኢትዮጵያዊያንም ኮርተንባቸዋል" ነው ያሉት፡፡

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ በመላክ ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመመከት የሚደረገው ዘመቻ አካል እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

"ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመነሳታቸው ጠላት ድል እየተመታ ነው" ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በግንባር በመሰለፍ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ድል እየመሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ጠላቶቿን አሸንፋ ወደ ከፍታ የምታደርገውን ጉዞ አጠናክራ እንደምትቀጥልም  ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመቀበል ለመጪው የገና በዓል ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡም አቶ አገኘሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም