አሸባሪው ሸኔ ከማንም በፊት የኦሮሞን ህዝብ ለማጥቃት የተነሳ የወንጀለኞች ስብስብ በመሆኑ በጋራ ክንዳችን እንታገለዋለን

244

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ሸኔ ከማንም በፊት የኦሮሞን ህዝብ ለማጥቃት የተነሳ የወንጀለኞች ስብስብ በመሆኑ በጋራ ክንዳችን ታግለን እናጠፋዋለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሃት “ኢትዮጵያን ለማፍረስ” ባወጀው ጦርነት አሸባሪው ሸኔም ይህንኑ ተልእኮ በመቀበል የጥፋት እንቅስቃሴውን ተቀላቅሎታል።

አሸባሪዎቹ ንፁሃንን ከመግደል በተጨማሪ የህዝብ መገልገያዎችን በመዝረፍና በማውደም በተለይም የህክምና ተቋማትና ትምህርት ቤቶችን እያወደሙ ነው።

እነዚህ የጥፋት ሃይሎች የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች መሆናቸውን አውጀው ግልጽ ዘመቻ በመጀመራቸው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እየተፋለሟቸው ይገኛሉ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ነዋሪው አቶ ኤፍሬም ተሰማ፤ አሸባሪው ሸኔ ከማንም በፊት የኦሮሞን ህዝብ ለማጥቃት የተነሳ የወንጀለኞች ስብሰብ በመሆኑ በጋራ ክንዳችን ታግለን ለማጥፋት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

አሸባሪው ሸኔ የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪ ሆኖ ህዝብ ለማጥቃትና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ተልእኮ የተቀበለ የወንጀለኞች ስብስብ መሆኑንም ገልጸዋል።

አሸባሪው ሸኔ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ አካባቢዎች በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ግፍና በደል እየፈፀመ በመሆኑ በጋራ ዘምተን ልናጠፋው ይገባል ያለው ደግሞ ወጣት ክፍሌ ታደለ ነው።

አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ከፍተኛ በደል መፈፀሙን ያስታወሱት አቶ ኤፍሬም አሁን ደግሞ ከአሸባሪው ሸኔ ጋር በመነሳት ለዳግም በደል እየተዘጋጀ በመሆኑ በጋራ ትግላችን ልናስወግደው ይገባል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ለኦሮሞ ህዝብ መብት ሲታገሉ የነበሩ በርካታ ወጣቶችን በማሰርና በመግደል ጭምር ወንጀል ሲፈፅም የነበረ ሃይል መሆኑን የጠቀሰው ወጣት ክፍሌ ለዳግም በደልና ግፍ እድል የሚሰጠው ማህበረሰብ ሊኖር አይችለም ብሏል።