አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ እስከሚጠፉ አካባቢያችንን እየጠበቅን ልማታችንን እናፋጥናለን

102

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገር ለማፍረስ የተነሱት አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ እስኪጠፉ ድረስ አካባቢያችንን እየጠበቅን ልማታችንን እናፋጥናለን ሲሉ በኦሮሚያ ክልል የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ነዋሪዎቹ "ጋቸና ሲርና" ወይም "የሠላም ዘብ" በሚሰኝ አደረጃጃት አካባቢያቸውን ከጥፋት ሃይሎች በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአሸባሪ ቡድኖቹ ግብዓተ መሬት እስከሚፈጸም ለመከላከያ ሠራዊቱና ለሌሎች የጸጥታ አካላት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡  

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ ነዋሪው አቶ ኦልማ ፈዬራ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ አካባቢውን በመጠበቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አካባቢያቸው ከጸጥታ ስጋት ነጻ እንዲሆንና ጸጉረ ልውጦች ገብተው ሠላማቸውን እንዳያደፈርሱ እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

"ሁለቱ አሸባሪ ቡድኖች ህወሓትና ሸኔ እስከሚደመሰሱ እረፍት የለንም፤ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግም ዝግጁ ነን" ብለዋል።

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የኢሉ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃኑ ቱራ በበኩላቸው በኢኮኖሚው ግንባር አገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታስገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ለመተካት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አገሪቷ በምግብ ፍጆታ ራሷን እንድትችል ለማድረግ በመትጋት ላይ መሆናቸውንም እንዲሁ፡፡

ከእርሻ ስራቸው ጎን ለጎንም በአካባቢያቸው ጸጉረ ልውጥ እንዳይገባ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን አካባቢያቸውን በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በ"ጋቸና ሲርና" ወይም የሠላም ዘብ በመሆን አካባቢያችንን እየጠበቅን ነው ያሉት ደግሞ ወሊሶ ከተማ ነዋሪው ታደለ ኢዶሳ ናቸው።

ሕዝቡ በአንድ ልብ፣ በአንድ ሃሳብ ሆኖ አገሩን በመታደግ ላይ በመሆኑ አሸባሪዎቹ ሸኔና ህወሓት የሚጠፉበት ቀን ሩቅ አይደለም ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።

የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪ የሆነው የሸኔ ቡድን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ አሰቃቂ ድርጊት በመፈጸም ታሪክ ይቅር የማይለው ተግባር ፈጽሟል ብለዋል።

ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአንድነት በመቆም የጋራ ሠላሙን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል ሲሉም አመልክተዋል፡፡

ኅብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅና ለሰራዊቱ ያለውን ድጋፍ በተለያየ መልኩ በመግለጽ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም