በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት የደረሰባቸውን ቅርሶች ለመጠገን ልዩ እቅድ ወጥቶ መሰራት አለበት

65

ህዳር 27/2014 በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት የደረሰባቸውን ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ለመጠገን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ልዩ እቅድ አውጥቶ መስራት አንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርን የ2014 እቅድ ገምግሟል።

በአዲሱ አደረጃጀት ከሌላ ተቋም ወጥቶ ራሱን በማደራጀት ላይ የሚገኘው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የአስር እና ዓምስት አመት እንዲሁም ለ2014 ዓ.ም የያዘቸውን እቅዶች ለቋሚ ኮሚቴው አስረድቷል።

በ2014 ዓ.ም ተቋሙ በትኩረት ለመስራት ከያዛቸው እቅዶች መካከል የስፖርትና በባህል ልማት፣ ተቋማዊ ግንባታ፣ በብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ፣ የባህል ጥናትና ምርምር ይጠቀሳሉ።

በእቅዱ መሰረት የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ ቋንቋና ታሪካዊ እሴቶች በስፋት ለማጥናትና ለማበልጸግ ይሰራል ተብሏል።

በቀረበው እቅድ ላይ ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን በማንሳት ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የባህል ብዝሃነትና ሌሎች እሴቶችን ለማጎልበት ሊሰራ ይገባል ብሏል።

ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ እሴቶችን ቁልፍ ተግባሩ አድርጎ እንዲሰራም ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ያለው አሸባሪው ህወሃት ጦርነት ከፍቶ ጉዳት ያደረሰባቸውን ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች እንዲሁም ተፈጥሯዊ ሃብቶችን ለመጠገን ልዩ እቅድ በማውጣት እንዲሰራም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ተቋሙ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ ዜጋን ለመቅረጽ ከታች ጀምሮ የመስራት ሃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን ለማጎልበት ባህላዊ እሴቶችን፣ ቱሩፋቶችንና ሌሎች አንድነትን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ፤ ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ አስተያየቶችን በእቅዳችን በማካተት እንሰራለን ብለዋል።

በተለይም ኢትዮጵያዊ አንድነትና ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት በትኩረት እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ባህላዊ ተቋማትንና ስታዲየሞችን ጨምር መልሶ ለመገንባት እቅድ አውጥተን እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ የቋሚ ኮሚቴውን አስተያየት በማካተት

እቅዱን እንደገና በማየትና አዳዲስ ፈጠራዎችን በመጨመር እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም