ዳያስፖራው የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ ሚናውን እንዲወጣ መንግሥት ጥሪ አቀረበ

163

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27/2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራ በቱሪዝም ዘርፍ የደረሰውን ጉዳት ዳግም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝበት ዕድል እንዲፈጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸማቸው ጅምላ ጭፍጨፋዎች በትክክል ዘር ማጥፋት የሚያሰኙ ወንጀሎችን መፈጸሙን ይፋ አድርጓል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ የምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች በሰጡት መግለጫ በወራሪው ቡድን ከተጎዱ ዘርፎች ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ የሆነውን ቱሪዝም ጠቅሰዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ወረራ ባደረገባቸው አካባቢዎች የቱሪስት መዳረሻዎች ለጉዳት በመዳረጋቸው ኑሮውን በቱሪዝም ፍሰት ላይ ያደረገው የማኅበረሰብ ክፍል ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ተዳርጓል ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ የሽብር ቡድኑ ወረራ ፈጽሞባቸው ከተለቀቁ ሥፍራዎች በቅርሶችና ባሕላዊ ሀብቶች ላይ መጠነ-ሰፊ ጉዳት  መድረሱን ጠቅሰዋል።

በደቡብ ጎንደር ብቻ ስድስት የእምነት፣ ሁለት የባህልና ቱሪዝም ተቋማት እና 20 የቱሪዝም አገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ላይ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራዎች መካከልም በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝም ፍሰት ሙሉ በሙሉ በመቆሙ ፓርኩ ያገኝ የነበረውን ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ማጣቱን ተናግረዋል።

ይህም በመሆኑ ኑሮውን በቱሪስት መዳረሻዎች ላይ ያደረገው ማኅበረሰብ የቱሪስት ፍሰት በመቆሙ ሳቢያ ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማጣቱን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በመንዝ ጓሳ፣ በቦረና ሳይንት ወረሂመኑ፣ አቡነ ዮሴፍ፣ በጉና እና መሰል የማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራዎች በወራሪው ቡድን ምክንያት መጠነ-ሰፊ ጉዳት መድረሱን አውስተዋል።

እንዲሁም በአፋር ክልል ነጻ በወጡ አካባቢዎች በተደረገ ቅደመ ምልከታ አገር ከክልሉ በዓመት ይሰበሰብ የነበረ 25 ሚሊዮን ብር በጦርነቱ ምክንያት አጥታለች።

በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የመንግሥት አብይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም አንስተዋል።

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በሚገኙበት ሥፍራ የደረሰው ጉዳት ዝርዝር ጥናት ቢፈልግም የጥገና ድጋፍ ለማድረግ ከወዲሁ ቃል የገቡ አገራት መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በወረራ ውስጥ ከነበሩ አካባቢዎች የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ ለጉዳት የተዳረገ ዘርፍ መሆኑን ተከትሎ ዘርፉን ለማነቃቃት ዝግጅት እየተደረገ ነው፤ የደረሰው ጉዳትም እየተጠና ነው።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለአገሩ እያበረከተ ካለው ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ በተጨማሪ ወደ አገር ቤት በመግባት እውነታውን ለማሳየት የተጀመረው ንቅናቄ እንዲሳካ መንግሥት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል።

በቱሪዝም ዘርፍ ከደረሰው ቁሳዊ ጉዳት ባሻገር በሥራ እድል ፈጠራና በማኅበረሰቡ ስነ-ልቦና ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በርካታ ቁሳዊ እና የማኅበራዊ ምጣኔ ሀብት ጉዳት በመድረሱ ጉዳቱን ለማካካስ የሁሉም ማኅበረሰብ የጋራ ትብብር ያሻል ብለዋል።

በዚህም የቱሪስት መዳረሻዎችን በመጠገን ዘርፉን ማነቃቃት፤ በአገርም ሆነ በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሌሎች ግንባሮች እንዳደረገው ሁሉ ተጋድሎ እንዲያደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የወገን ጥምር ጦር ባደረገው ተጋድሎ አሸባሪው ህወሓት በሁሉም ግንባሮች እየተሸነፈ ሲሸሽ ለሰሚ የሚዘገንኑ እና የቡድኑን እኩይ ተግባር በይፋ ያረጋገጡ የጅምላ ጭፍጨፋና ውድመቶች እያደረሰ  ነው ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ዘር ማጥፋት የሚያሰኙ ጅምላ ጭፍጨፋዎችን በአማራ እና በአፋር ክልሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ ማድረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ቀደም ሲል በቆቦ፣ ውጫሌ፣ ውርጌሳ፣ አጋምሳ፣ ጋሊኮማ፣ ጭና፣ ኮምቦልቻና ሌሎች አካባቢዎች ከፈጸማቸው ጅምላ ጭፍጨፋዎች ባሻገር ከሰሞኑ በጋሽና እማ በሸዋ ግንባሮች በአንፆኪያ ገምዛ ጅምላ ጭፍጨፋ ፈጽሟል፤ የጅምላ መቃብሮችም ተገኝተዋል ብለዋል።

የውጭ መገናኛ ብዙሃን እና ለሰብዓዊ መብት ቆመናል የሚሉ አካላት ይህን ወንጀል ቢረዱም እያጋለጡ አለመሆኑንም ነው የተናገሩት።

የሽብር ቡድኑን ወንጀሎች በገለልተኛ አካል በማጣራት ዓለም እንዲገነዘበው ይደረጋል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም