በግንባር እየተቀዳጀን ያለነውን ድል በግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይም እየደገምናቸዉ እንገኛለን

72

ህዳር 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) “በግንባር እየተቀዳጀን ያለነውን ድል በግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይም እየደገምናቸዉ እንገኛለን” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በከተማዋ ከፑሽኪን አደባባይ ጎተራ፣ ከቦሌ ሚካኤል ቡልቡላ፣ ከቦሌ አየር ማረፊያ ጎሮ እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅትም “ኢትዮጵያ በታሪኳ ገጥሟት የማያውቅ ፈተና ውስጥ ሆና በድል አድራጊነት መንፈስ ፈተናውን እየተወጣች ትገኛለች” ብለዋል፡፡ ከበርካታ ፈተናዎች አንዱ በድል እየተጠናቀቀ የሚገኘው የግንባሩ ፈተና መሆኑን ጠቅሰዋል።

“በግንባር እየተቀዳጀን ያለነውን ድል በከተማው ውስጥ በጀመርናቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይም እየደገምናቸዉ እንገኛለን” ያሉት ከንቲባዋ፤ በከተማዋ የሚገኙ አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እየተከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ በተለየ እልህና ወኔ የድል አድራጊነት መንፈስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ይሄንን የምናደርግበት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ እንደ ሀገር ያለንበትን ሁኔታ ከመገንዘብ የመነጨ ሲሆን፤ ለፕሮጀክቶች ስኬት እዚህ ደረጃ መድረስ የግንባሩ ድል ትልቅ አቅም ሆኖናል” ሲሉ ገልጸዋል።

በተለይም መንገዶች በሚገነቡበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች በከፍተኛ ተነሳሽነትና የሀገር ፍቅር ስሜት በወሰን ማስከበር ሂደት ውስጥ ያሳዩት ተባባሪነት እጅግ የሚያሥመሰግን ተግበር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ የመንገዶች ባለስልጣን ሀላፊ ኢንጅነር ሞገስ ጥበቡ በበኩላቸው ፕሮጀክቶቹ የከተማውን የመንገድ ሽፋን በማሳደግ የትራፊክ ፍሰት እንደሚያሻሽሉ ጠቅሰዋል።የመንገደቹ ግንባታ ወጪ ሙሉ በሙሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሽፋን የተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም