ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚውል 640 ሺህ ዶላር በሎስ አንጀለስ ተሰበሰበ

122

አዲስ አበባ ህዳር  27/2014 /ኢዜአ/ በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ በአንድ ምሽት በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል 640 ሺህ ዶላር ተሰበሰበ።
ከትናንት በስቲያ በተካሄደው መርሃ ግብር በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ፣ በሎስ አንጀለስ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችን ጨምሮ 500 ሰዎች ተሳትፈዋል።

በገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱ በአንድ ምሽት በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች 640 ሺህ ዶላር መሰብሰቡን ኢዜአ ከድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ገንዘቡ በጨረታ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ በጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊና በሌሎች ታዋቂ  ሰዎች ስም እንዲሁም በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮች መሰባሰቡ ተገልጿል።

የተሰበሰበው ገንዘብ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላክ ኮሚቴው አስታውቋል።

በሎስ አንጀለስ እና አካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ መስኮች ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውም ተነግሯል።

ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ሳክሪሜንቶ ከተማ በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር 250 ሺህ ዶላር መሰብሰቡ የሚታወስ ነው።

በአንድ ሳምንት ውስጥ በካሊፎርኒያ ግዛት በሚገኙት ሎስ አንጀለስ እና ሳክሪሜንቶ ከተሞች በተካሄዱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች በድምሩ 890 ሺህ ዶላር መሰብሰብ ተችሏል።

በቀጣይ መሰል የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች እንደሚካሄዱም ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና ከትናንት በስቲያ የኢትዮ-ካናዳዊያን ኔትወርክ ለማኅበራዊ ድጋፍ /ኢክናስ/ የቶሮንቶ ቻፕተር በካናዳ ቶሮንቶ ከተማ አሸባሪው ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከ250 ሺህ በላይ የካናዳ ዶላር መሰብሰቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም