ለሃገር መከላከያ ሠራዊት ደማቸውን ብቻ ሳይሆን ህይወታችንንም እንሰጣለን

80

አሶሳ ፤ ህዳር 26/2014 (ኢዜአ) ለሃገር መከላከያ ሠራዊት ደማቸውን ብቻ ሳይሆን ህይወታቸውንም ለመስጠት መዘጋጀታቸውን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የአሶሳ ከተማ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተናገሩ።
የከተማው የንግዱ ማህበረሰብ አባላት   ለመከላከያ ደም በመለገስ ድጋፍ እያረጉ ነው።

ደማቸውን ለሠራዊቱ ሲለግሱ ኢዜአ ካነጋገራቸው የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መካከል አቶ መስፍን እንድሪስ ፤አሸባሪው ህወሃት ሀገር ለማፍረስ ከሚከተላቸው መንገዶች አንዱ በተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ እንዲማመረር በማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ሸማቹ  ብቻ ሳይሆን ህጋዊው የንግዱ ማህበረሰብ ጭምር ተጎጂ ነው ብለዋል፡፡

የአሸባሪው ህወሃት ሴራ በግንባር እየተፋለመ ኢትዮጵያን እያስቀጠለ ለሚገኘውን የሃገር መከላከያ ሠራዊት ታላቅ አክብሮት እንዳለቸው ነው የገለጹት፡፡

ለመከላከያ ሠራዊት የማደርገው ደም ስጦታ ዝቅተኛው ነው ያሉት አቶ መስፍን፤ በገንዘብም ከሚያደርጉት እገዛ ባለፈ እስከ ግንባር ከሠራዊቱ ጎን  የመቆም ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ሀገራችን እንድትቀጥል መከላከያ በህዝብ የተጣለበትን ሃላፊነት በሚገባ እየተወጣ ነው ያለው ደግሞ ወጣቱ ነጋዴ  አብዱራዛቅ እስማኤል ነው፡፡

የንግድ ስራ የምናካሂደው ሃገር ስትኖረን ነው ያለው ወጣቱ፤  በጦር ግንባር ተገኝቼ ከሃገር መከላከያ ሠራዊቱት ጋር ባልዘምትም ደሜን ለሠራዊቱ በመስጠት ደጀን መሆን የግድ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አቶ ጎይቶም መላከ በበኩላቸው፤ ለሃገር መከላከያ ሠራዊት ደም ሲለግሱ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ አስታውሰው፤ አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ እና በፌደራል ፖሊስን ጨምሮ በኢትዮያውያን ላይ ያደረሰው ግፍ አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ዘምተው ሰራዊቱን በመምራት ት ያስመዘገቡት ድል እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል።

ለጀግናው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ደም ብቻ ሳይሆን ህይወቴን በስጥ ደስተኛ ነኝ ብለዋል አቶ ጎይቶም።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንግድ እና የዘርፉ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ እንድሪስ አህመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ እስከ ከፍተኛ የውትድርና ሙያ ያላቸው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በሙያቸው ሃገር ለመታደግ የዘመቱም እንዳሉም እንዲሁ፡፡

ምክር ቤቱ ባለፈው አንድ ወር ብቻ ከንግዱ ማህበረሰብ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና  በዓይነት   ድጋፍ አሰባስቦ ለሃገር መከላከያ ሠራዊትና  እንዲሁም ለአማራ፣ አፋር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተፈናቃዮች ማስረከቡን አስታውቀዋል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ የተሰበሰበው ድጋፉ ያለማንም ቅስቀሳ በንግድ ማህበረሰቡ ተነሳሽነት እየተከናወነ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ሽብርተኛውን ህወሃት አንድታችንን በማፍረስ ኢትዮጵያ ለመበታተን ዘምቶብናል ያሉት ሼህ እንድሪስ፤ ይህን ጠላት መመከት ለመከላከያ ሠራዊታችን ብቻ የሚተው አይደለም ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ የሽብርተኛው የጥፋት ሰራ ከሽፎ  ሃገር ወደ ቀደመ ሠላሟ እስክትመለስ የንግዱ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲጠናከር ሶስተኛ ዙር የድጋፍ ማሰባሰቢያ እቅድ አዘጋጅቶ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም