ዩኒቨርሲቲው 1ሺ ኩንታል ባላይ የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ

252

ሐረር (ኢዜአ) ህዳር 26/2014 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 1ሺ 200 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ለምስራቅ ሐረርጌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ድጋፍ አደረገ።
ዩኒቨርሲቲው በእርዳታ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ የሚተካ ምርት በመስኖ በማልማት የውጭ ሀገር ተጽዕኖን ለመከላከል እየሰራ መሆኑንም  አስታውቋል።

ለምስራቅ ሐረርጌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ድጋፍ ያደረገው የስንዴ ምርጥ ዘር ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት መሆኑም ተገልጿል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ ለማ በእዚህ ጊዜ እንዳሉት ከውጭ የእርዳታ ስንዴ ለማግኘት የተለያየ ተጽዕኖ ሲደረግ ይታያል።

ለዚህም ዋነኛው መፍትሄ ሀገር ያላትን የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰው ሀይልና ቴክኖሎጂን በአግባቡ በመጠቀም በምግብ ራስን መቻል መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም የውጭ ተጽዕኖን መቋቋም ባለፈ ለስንዴ ግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት እንደሚቻል ነው ዶክተር ተስፋዬ የገለጹት።

እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ በዩኒቨርሲቲው በኩል ካለፈው ዓመት ጀምሮ የምርምር እና የማስፋፋት ሥራዎች እየተሰሩ ነው።

ከእዚህ በተጨማሪ የግብርና ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም የምርጥ ዘር እጥረት እንዳይከሰት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌታሁን ንጋቱ እንዳሉት፣ በዞኑ የአገርን ህልውና ለማስቀጠል ከሚከናወኑ ተግባራት ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

ለእዚህም በበጋ የመስኖ ልማት በ27 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምረት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በልማቱም ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለምግብነትና ለብዜት የሚሆኑ 1ሺህ 200 ኩንታል የስንዴ ዘሮችን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

“በቀጣይም ስንዴውን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት እንዲሁም ክትትልና ድጋፍ በማድረግ አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ ይሰራል” ብለዋል።

ለዚህም አስፈላጊው የቦታ መረጣና የመሬት ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን አቶ ጌታሁን ጠቁመው፣ ድጋፉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በተጨማሪ በዞኑ ያለውን የምርጥ ዘር እጥረት እንደሚያቃልል ተናግረዋል።

የቀርሳ ወረዳ የመስኖ ልማት ሥራ ሃላፊ አቶ ፉዓድ መሀመድ እንዳሉት የወረዳው አርሶ አደሮች ማሽላና በቆሎ ቢያመርቱም ስንዴ የሚያገኙት በእርዳታ በመሆኑ የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ አልተቻለም።

በተለይ በአሁኑ ወቅት በወረዳው ከ300 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ስንዴ በበጋ መስኖ ለማልማት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

“በዞኑ የተጀመረውን የበጋ ስንዴ ምርታማነት ለማሳደግ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ስራውን በትኩረት እየሰራ ነው” ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲ በእጽዋት ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ አቶ አጥላባቸው መኮንን ናቸው።

በተለይ ዝናብ አጠር ለሆኑ በቆላማ አካባቢዎች ተስማሚ የሆኑና በሄክታር ከ50 እስከ 60 ኩንታል ምርት የሚሰጡ 21 የስንዴ ዝርያዎችን ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የምርምር ተቋም በማስመጣት ከአርሶ አደሩ በተጨማሪ በአካባቢው የማላመድ ሥራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በምርምር ያገኘቸውንና የተሻለ ምርት የሚሰጡትን “ቡቡ” እና “ሁንደኔ” የተባሉ ሁለት የድንች ዝርያዎችን በቀጣይም በሐረማያ ወረዳ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ማሰራጨት በበጋ ወራት በመስኖ አልምተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑንም ተገልጿል።