የጠላቶቻችን ማርከሻ ዋና ጉልበት በጽኑ መሰረት ላይ የተመሰረተው አንድነታችን ነው

252

ጎንደር ፤ ህዳር 26/2014(ኢዜአ) ”የእኛ ኢትዮጵያውያን የጠላቶቻችን ማርከሻ ዋና ጉልበት በጽኑ መሰረት ላይ የተመሰረተው አንድነታችን ነው” ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡
”የአንድነት ደወል በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ በጎንደር ከተማ ታላቅ ህዝባዊ የንቅናቄ መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ሚኒስትሩ በመድረኩ እንዳመለከቱት፤  የኢትዮጵያ ጽኑ መሰረት የሆነው አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርጉ ህዝባዊ ውይይቶች ዛሬም ሆነ ነገ አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው  አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከሰራቸው  ተንኮሎችና ሴራዎች አንዱ ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝቦች መካል አንድነት እንዳይኖር ማድረግ ነው ብለዋል።

ለዚህም ባለፉት 27 ዓመታት የፈጸማቸው  እኩይ ተግባራት  ተጠቃሽ መሆናቸውን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፤  አሁን ላይ ኢትዮጵያውያን የጠላቶቻችን ድል መንሻ ጉልበት አንድነታችን ነው ሲሉ ተናገረዋል።

”ህዝቡ ወራሪውን ሃይል ለመመከት  ከደጀንነት ጀምሮ በግንባር ጭምር በመሰለፍ ያደረጋቸው ተጋድሎዎች የአንድነቱ ማሳያ ነው  ” ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር  ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ናቸው፡፡

በዚህ ላይ ህዝቡ  ያሳየውን  ተሳትፎ በማጠናከር ከተማውን ከሰርጎ ገቦችና ጸጉረ ልውጦች እንዲሁም ከጠላት ድብቅ ሴራ ነቅቶ እንዲጠብቅም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ወጣቱ ሀገሩን ከወራሪና ከውጪ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት እንዲከላከል የሀገር አለኝታና መከታ ከሆነው መከላከያ ሰራዊት እንዲቀላቀልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ  ከጎንደር ከተማ፣ ሰሜን፣ ማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ የህዝብ ወኪሎች፣ ባለሀብቶች፣ ነጋዴዎች፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡