ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለህልውና ዘመቻው ድጋፋቸውን እናጠናክረው ይቀጥላሉ

80

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ህዳር 26/2014 በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚንቀሳቀሱ ሀገር አቀፍ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የህልውና ዘመቻው በስኬት እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።
በውይይቱ በድሬዳዋ አስተዳደር የሚንቀሳቀሱ ገዢው የብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ 10 ሀገር አቀፍ ተፎካካሪ ፓርቲዎች  በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተሳተፉበት የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተወያይቶ ባወጣው ባለ 5 ነጥብ የአቋም መግለጫ  አውጥቷል።

ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ በሀገር ላይ የተደቀነውን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ ከመንግስት ጋር በመሆን እንደሚሰራና አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉ እንደሚቀጥል አረጋግጧል፡፡

ከሀገርና ከህዝብ በላይ የሚቀድም አጀንዳ ስለሌለ ሀገር ለመበተን የተነሳውን አሸባሪው ህውሓትና ተላላኪዎቹ እያደረሱ ያለውን ጥፋት ለማስቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ  አስታውቀል።

ከዚህም ባሻገር ፓርቲዎቹ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን አስተባብረው የድሬዳዋ ሰላምና ፀጥታ መጠበቅ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳትና ብሔራዊ የልማት አጀንዳዎች እንዳይቋረጡ ለማገዝ እያደረጉ ያለውን እንደሚያጠናክሩም በመግለጫቸው አመላክተዋል።

ለአሸባሪ ህወሓት በመወገን በዓለም መገናኛ ብዙሀን የሚሰራጩ የሐሰት ወሬዎችን በሁሉም መገናኛ ብዙሀንና ተግባቦት በመመከት የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ እንደሚተጉም አስታውቀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የጀመሩት ዓለም አቀፍ የተቃውሞ ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ታላቅ አክብሮት የተናገሩት የምክር ቤቱ አባላት፣ መንግስት ሀገርን ለማዳን የሚያወጣቸው አቅጣጫዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ህዝቡን፣ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን እንደሚያስተባብሩ ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢዜማ የድሬዳዋ ተወካይ አቶ ዮናስ በትሩ እንደተናገሩት፣ ሀገርን ለማዳን ግንባር መዝመትን ጨምሮ አስፈላጊው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

"ጠንካራ ሕብረትና አንድነት በመፍጠር ሀገርን ለማሻገር ያለልዩነት የተቀናጀ ጥረት እናደርጋለን" ብለዋል፡፡

"ሀገር ሲኖር ሁሉም ነገር ይኖራል፤ፖለቲካና ስልጣንም የሚኖረው ሀገር ሲኖር ነው" ያሉት አቶ ዮናስ፣ ሀገርን ለማዳን፣ የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋምና የተጎዱትን ለመርዳት ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራሮች ቀደም ሲል ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስንቅ አዘጋጅተው መላካቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም