የምዕራባውያን ፀሃይ እየጠለቀች ይሆን….?

70

የምዕራባውያን ፀሃይ እየጠለቀች ይሆን….?

መግቢያ

ዴሞክራሲን ጨምሮ የሰብዓዊነትም ሆነ የሁሉንም ነገር ትክክለኛነት የምንመዝነውም ሆነ የምናጸድቀው እኛ ነን ከዚህ ውጭ ያለው ትክክል አይደለም የማለት አባዜ የተጸናወታቸው አንዳንድ ምዕራባዊያን ከነሱ ይሁንታ ውጭ የሚከናወኑ ምርጫዎች፣ ዘገባዎች፣ ልማቶችና ሌሎችም ተቀባይነት የላቸውም። በጎ ነገራቸውን ማየትም ሆነ መስማት አይፈልጉም

ከነሱ ፈቃድ ባፈነገጠ መልኩ ስለሚንቀሳቀሱት የምስራቁ ዓለም ሃገራት ትብብርና አጋርነት ሲዘገብ ሲወራ መስማት ምርጫቸው እንዳልሆነ ግዙፎቹ የመገናኛ ብዙሃን ኩባንያዎቻቸው የተዛቡ ዘገባዎች ማሳያ ናቸው።  እነሱ ሊያነቧቸው ከማይፈሉጓቸው መጽሃፍት መካከል ደግሞ ቻይና ዓለምን ስትገዛ-የምዕራቡ ዓለም መጨረሻ እና የአዲስ ዓለም አቀፍ ሥርዓት መወለድ” በሚል ርዕስ በማርቲን ዣክ የተፃፈው መጽሃፍ አንዱ ነው።ታዲያ ምዕራባውያን ባይወዱትም ተገደው እንዲያነቡት አድርጓቸዋል። ጉዳዩ የተቀናቃኛቸው የቻይና መነሳት በመሆኑ።  

ይኸው መጽሃፍ በመቶ ሺዎች ኮፒ የተሸጠ ከመሆኑ ሌላ የዓለም አቀፍ ምርጥ ሽያጭ ሰነጠረዥ ውስጥ መካተቱና በ11 የተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለንባብ መብቃቱ ምዕራባውያን ሳይወዱ እንዲያነቡት ሆኗል። መጽሃፉ በቻይና ኃይል እየተቀረጸ ያለውን ዓለም ለመረዳት ጠቃሚ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ዓለም በሁለት ጎራ ተከፍላ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍጥጫ ውስጥ በነበረችበት በዘመነ ቀዝቃዛ ጦርነት የአሜሪካ ዋነኛ የስጋት ምንጭ ሩሲያ ነበረች። እ.ኤ.አ በ 1989 የበርሊን ግንብ ሲፈርስ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ የቀድሞዋ ሶቭዬት ኅብረት ተንኮታኩታ ወደ 15 አገራት ተከፋፍላለች።

የያኔው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ (ትልቁ) የሶቭዬት ኅብረት መሪ ከነበሩት ሚኻኤል ጎርባቾቭ ጋር እ.ኤ.አ በ 1989 በማልታ ተገናኝተው ዓለምን የቀየረ ውይይት አድርገዋል። በማልታው ጉባዔም ሁለቱ አገራት ከተቀናቃኝነት ወጥተው በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል። ከዚህ ባለፈም በሦስተኛ ዓለም አገራት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ስለሚፈቱበት መንገድ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል። በዛም የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ፍፃሜውን አገኘ።     

ቀዝቃዛው ጦርነት አክትሞ የሁለት ጎራ ዘመን ሲያበቃ ዓለም አንድ ሆነች። አሜሪካም ብቸኛዋ ልዕለ ኃያል አገር ሆና ብቅ አለች። ግሎባላይዜሽን ደግሞ ቀጣዩ ባለተራ ሆነ። ዓለም በቴክኖሎጂ፣ በፖለቲካ-ኢኮኖሚና በሪዕዮተ ዓለም ወደ መቀረራብ ያመራች መሰለች። ምዕራባውያን 'ድሆች' በድህነታቸው እንዲቀጥሉ 'ባለጸጎችም' ይበልጥ እንዲበለጽጉ መስራትን ገፉበት። ሂደቱም ለሩብ ክፍለ ዘመን ቀጠለ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ነገሮች እየተለዋወጡ ስለመሆናቸው በርከት ያሉ ጠቋሚዎች መታየት ጀምረዋል። ይህን የተገነዘበው ዘ ኢኮኖሚስት መጽሄት የዛሬ 15 ዓመት ገደማ “አፍሪካ ወደ ምሥራቅ እያማተረች ነውን? ሲል በፊት ገጹ ይዞት የወጣው ጽሁፍ ያለምክንያት አልነበረም። በእስያ አገራት የታየው ፈጣን ዕድገት የአፍሪካውያንን ቀልብ መሳብ መቻሉ ደግሞ በምክንያትነት አስቀምጦ ነበር።

በሁለንተናዊ ዕድገታቸው ልቀው የሚወጡ አገራት (Emerging Countries) ብቅ ብቅ ማለት በምዕራባውያን የተወደደ አልሆነም። ለወትሮው ምዕራባውያን ትኩረት ያልሰጧት አፍሪካ መነቃቃት ማሳየቷ ደግሞ ፍጹም አልዋጥ ብሏቸዋል። በአንፃሩ የምዕራቡ ዓለም አሁን ድረስ የቅኝ ግዛት ዘመንን ከሚያስታውስ የዛገ ፖሊሲ ጋር ተጣብቋል።

የቻይና የልማት አማራጭነት

አሁን አሁን አሜሪካ ራሷን ከዕውነታው ጋር ያስማማች አትመስልም። የአፍሪካና የሌሎች አዳጊ አገራት ለውጥን መገንዘብ ተስኗታል። ሃቁን ግን አፍሪካውያን ለውጥ ላይ መሆናቸው ነው። የቻይና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የመተማመን ጥጓ ከፍ ማለቱ ደግሞ ዕውነታውን ጎልቶ እንዲታይ ማድረግ ችሏል።  

ማርቲን ዣክ ቻይና በቅርቡ ልዕለ ኃያል አገር ትሆናለች ሲል በመጽሃፉ አስቀምጧል። ይህ ሲሆን ግን ይላል ፀሃፊው ምዕራባዊ ቅርጽ አይኖረውም። ቻይና እየፈረጠመች ስትመጣ የዓለም የኃይል ሚዛን ገጽታ በሚገረም ሁኔታ መቀያየር ጀምሯል። እናም አሁን ላይ ቻይና ለተቀረው ዓለም በተለይ ለአፍሪካና ለሦስተኛ ዓለም አገራት በብዙ መልኩ ከአማራጭም በላይ አስተማማኝ የልማት አጋር  መሆን ችላለች።  

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አፍሪካውያን ከተቀረው ዓለም ጋር በጋራ መከባበርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ትብብር መፍጠራቸው አዎንታዊ ለውጥ አስገኝቶላቸዋል። ይህ ደግሞ አፍሪካን አንድ እርምጃ ወደፊት መውሰድ ችሏል።

በአንፃሩ ምዕራባውያን በአገራት የውስጥ ጉዳይ ከመግባት አንስቶ እስከ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ዕቀባዎች የደረሰ ጫና በማድረግ የአፍሪካን የመልማት ተስፋ ለዘመናት ሲያጨልሙ ታይተዋል። በቅርቡ በባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያ ላይ የተጣለው ዕቅባም አንዱ ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ በ1960ዎቹ በአድሃሪው የሲያድ ባሬ መንግሥት ስትወረር አሜሪካ የኢትዮጵያን ወዳጅነት ዘንግታ ጀርባዋን መስጠቷ ታሪክ የማይረሳው ክህደት ነው። ኢትዮጵያ የፀረ-ሽብር ትግልን ጨምሮ በብዙ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ከአሜሪካ ጋር አጋር ሆና እየሰራች መሆኗ ለሁሉም ግልጽ ነው። ዳሩ ግን ታሪክ ራሱን ሲደግም በዚህ ፈታኝ ወቅት አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ አሁንም ክህደት ፈጽማለች። አሜሪካ የኢትዮጵያን ከቀረጥ ነፃ ዕድል ተጠቃሚነት ማለትም ከአጎዋ እንድትሰረዝ መወሰኗ ሳያንሳት አሸባሪው ህወሓትን በመደገፍ ጊዜው ያለፈበትን ጣልቃ ገብነቷን ልታሳይ ሞክራለች።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በቅርቡ ኬንያን ጨምሮ በሦስት የአፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝት አፍሪካውያን በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርጉ ለማበረታታት ያለመ ነበር። ነገር ግን ስኬት አልባ ሆኖ ተጠናቋል። ኢትዮጵያ አሁን ያጋጠማት ቀውስ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ በራስ አቅም እልባት የመስጠት መብቷ እንደተጠበቀ ሆኖ አሜሪካ ችግሩን ለመፈታት ገንቢ ሚና እጫወታለሁ ካለች መንግሥት በአዎንታ ሊቀበለው የሚችል ይሆናል። ያሞ ሆኖ አንቶኒ ብሊንከን የጉዳዩ ባለቤት ከሆነችው አገር ይልቅ ወደ ጎረቤት አገራት በመሄድ ኢትዮጵያን ሲዞሯት ሰንብተዋል።

በአንፃሩ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋን ዪ በዚህ ወሳኝ ወቅት አገራቸው ለኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኛ አጋርነትና ድጋፍ ለመስጠት አዲስ አበባ በመገኘት አረጋግጠዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቻይና በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ጠንካራ መተማመን በአካል ተገኝተው ከመግለጽ ባለፈ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አገራቸው እንድምትቃወም አረጋግጠዋል።

ከሰሞኑ በሴኔጋል መዲና ዳካር በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ የልማት ትብብር ፎረምም ቻይና ለአፍሪካውያን በእርግጥም የልማት አማራጭና አጋር መሆኗን አስመስክራለች። ምዕራባውያን የአፍሪካውያንን ድህነት ማባባስ ላይ በተጠመዱበት በአሁኑ ግዜ የቻይና መንግሥት የአሕጉሪቱን ህዝቦች ከድህነት ለማላቀቅ አጋዥ ይሆናሉ ያላቸውን አማራጭ ሃሳቦችን ይዞ ብቅ ብሏል። ቻይና አጎዋን የሚስተካከልታሪፍ ነፃገበያ አማራጭን (Green Lanes) ለአፍሪካ እነሆ ብላለች።  

ቻይና ለአፍሪካ አገራት ያቀረበችው ዕድል አፍሪካን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ ነው። በዚህም ማንኛውም ከቻይና መንግሥት ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያለው አገር ምርቶቹን ከቀረጥ ነፃ በብዛት የማስገባት ዕድል የሚያስገኝለት ይሆናል። በአንፃሩ ቻይና በየዓመቱ ከአፍሪካ አገሮች የምታስገባቸውን ምርቶች አሁን ካለበት 210 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወደ ግማሽ ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያሳድገው ታምኖበታል። የአሁኑ የቻይና እርምጃ ለኢትዮጵያ ትልቅ የምስራች ነው። ምክንያቱን ከአጎዋ ያጣችውን የገበያ ዕድል ዳግም የሚያስገኝላት በመሆኑ።

የምዕራቡ ዓለም ፀሃይ መጥለቅ

ለኃያላን መንግሥታት ትልቁ አደጋ በከፍታ ጫፍ ላይ እንዳሉ ሲያስቡ ነው ይላሉ ፀሃፊው ማርቲን ዣክ። እዚህ ላይ “ብሪታንያ ማዕበሉን ትገዛለች?” የሚለውን መዝሙር ማስታወሱ ግድ ይላል። ባለፈው ማክሰኞ ‘ፀሃይ አትጠልቅባትም’ ሲባልላት የነበረችው ታላቋ ብሪታኒያ በቅኝ ስትገዛት የነበረችው የካሪቢያን ደሴቷ ባርቤዶስን አጥታለች። ዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥም ከኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የባርቤዶስ ንግሥት መሆናቸው በይፋ አብቅቷል። ባርቤዶስም ነፃና ልዑላዊ አገር ሆናለች።

ይህ ደግሞ “ፀሃይዋ አትጠልቅም” ዓይነቱ ዘላለማዊ የኃያልነት ጥግ ለታላቋ ብሪታኒያ ከንቱ ውዳሴ እንደነበር በግልጽ አሳይቷል። በአጭሩ የባርቤዶስ ሉአላዊነት ይፋ መሆን የምዕራባውያን ፀሃይ መጥለቅ አንዱ ማሳያ ሆኖ ታሪክ ሰንዶታል።

ቻይና በጣም የረቀቀ እና የምዕራቡ ዓለም ሊረዳው የሚያዳግት የረዘመ ጨዋታ መጫወት ከጀመረች ዓመታትን አስቆጥራለች። ጉዳዩ በቻይናውያን ንቃተ-ህሊና የተገለጸ ስልት ሲሆን ይህን ለመፈጸም ቻይና የተለየ መንገድ እየተከተለች ስለመሆኗ የሚያመላከት ነው። 

በሥሩ 38 አገራትን ያቀፈው የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት (OECD) በዓለም ዙሪያ ባሉ የ 15 ዓመት ተማሪዎች ላይ ባደረገው ጥናት ያረጋገጠው ቻይናውያን ተማሪዎች በሁሉም የትምህርት መስኮች አሜሪካውያን ተማሪዎችን ማስከንዳታቸውን ነው። የዚህ አንድምታው የመጥለቅ ማሳያ ተደርጎ ከመውሰድ ውጭ ሌላ ሊሆን አይችልም።

ምዕራባውያን የአሜሪካ ኃያልነት መዳከም ሳይሆን የቻይና መነሳት በጣም እንደሚያስፈራቸው ጸሃፊው ይናገራሉ። ስለ አሜሪካ መዳከም ምዕራባውያን ብዙ ማውራት አለመምረጣቸውም ምክንያቱ ይኸው ነው። ለዚህም ይመስላል የሚጠሉትን የማርቲን ዣክ መጽሃፍን ምዕራባውያኑ ደጋግመው የማንበባቸው ምስጢር።

በመጽሃፉ የተነገራቸው አሁን ላይ ገሃድ እየሆነ መምጣት ሲጀምር አሜሪካውያን ቻይናን ከሩሲያ አሊያም ከየትኛውም አገር በላይ በስጋትነት መመልከታቸው። ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳደረባቸውም በሮናልድ ሬገን ኢንስቲትዩት የተካሄደ አዲስ የህዝብ አስተያየት ጥናት ያመለክታል።

እናም አሁን ላይ አሜሪካውያን የቻይናን ሁለንተናዊ ፈታኝነት በውል መገንዘብ የጀመሩ ይመስላሉ። በአሁኑ ግዜ 71 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን አገራቸው ከቻይና ጋር ወደ ወታደራዊ ግጭት ልታመራ ትቻላለች የሚል ፍራቻ አላቸው። በመጠይቁ ከተካተቱ ረፐብሊካን 79 በመቶ እንዲሁም 66 በመቶ ያህሉ ዴሞክራቶች ፍራቻውን ይጋሩታል።

የሬጋን አስተዳደር የቀድሞ የመከላከያ ኢንተለጀንስ ኤጀንሲ ባለስልጣን የነበሩት ሚካኤል ሴኮራ በቅርቡ ለፎክስ ኒውስ እንደገለጹት አሜሪካ በቴክኖሎጂ ቻይና ላይ መድረስ አይቻላትም። የባይደን አስተዳደር የተለየ የብሄራዊ ቴክኖሎጂ አማራጭ ስትራቴጂ እስካላቀረበ ድረስ የቱን ያህል ገንዘብ ለምርምር እና ልማት ቢያፈስ ቻይና ላይ መድረስ ዳገት ይሆንበታል ብለዋል።

የቡሽ አስተዳደር ዓለም እንደ አሜሪካውያን ፍላጎት እንደገና እንደምትቀረጽና ይህ ደግሞ የቀዝቃዛው ጦርነት እውነተኛ ውርስ ይሆናል ብሎ አስቦ ነበር። ዳሩ ግን እሳቤው ፍጹም ስህተት መሆኑን አሁን ላይ ድፍን ዓለም የተገነዘበው ይመስላል። ምክንያቱም የአሜሪካ ኃይል በእርግጥም እያሽቆለቆለ መምጣት ጀምሯልና። በዋናነት የሚነሳው ግን አገራት እያደጉ መምጣታቸው ሲሆን ከሁሉም በላይ ግን የቻይና ኃያል አገር ሆና ብቅ ማለቷ ነው።

ምዕራባውያን ዘመናዊነት (Modernity) አንድ ዓይነት ብቻ ነው ብለው ያስባሉ። የምዕራቡ ዓለም ዘመናዊነት ብቻ። በማደግ ላይ ያሉ አገራት ወደ ምዕራባውያን ዓይነት ማኅበረሰብ በተመሳሳይ አቅጣጫ በሚያመሩ መወጣጫዎች ላይ ናቸው ብለው ያምናሉ። ማርቲን ዣክ የቻይና ኃያል አገር ሆና ብቅ ማለት የምዕራባውያን ዓይነት የዘመናዊነት ቅርጽ አይኖረውም ያሉትም ለዚህ ነው። እናም አሜሪካ ለወትሮው ለአፍሪካ ትመክረው የነበረውን መዋቅራዊ ማስተካከያ (Structural Adjustment) አሁን ላይ ፀሃይ ጠልቃ ሳይጨልምባት ለራሷ የሚያስፈልጋት ይመስላል።

SEE LESS

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም