የአዳማ ከተማ ወጣቶች ከሰርጎገቦች በንቃት እየጠበቁ ነው

71

አዳማ ህዳር 26/2014 (ኢዜአ) የአዳማ ከተማ ወጣቶች ከተማቸውን ከአሸባሪዎችና ሰርጎገቦቻቸው ቀን ከለሊት የሰላምና ፀጥታ ስራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን አስታወቁ።
በከተማዋ  በለሊት በጥበቃ ስራ ከተሳታፉት ወጣቶች መካከል ወጣት ዘሪሁን ፍቃዱ እንደገለፀው አዳማን ከአሸባሪዎችና ሰርጎገቦቻቸው ለመጠበቅ ቀን ከለሊት የሰላምና ፀጥታ ስራዎችን ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን እያከናወኑ ነው።

ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያ ተፈፃሚነትና ውጤታማነት ወጣቶች ወታደራዊ ሙያ ጭምር ወስደን  ፀጥታ የማስከበር ስራ እየሰራን ነው ብሏል።

በተለይም የተሽከርካሪዎችና የተገልጋዩን ማህበረሰብ ፍተሻና የአካባቢ ፀጥታ ማስከበር ላይ በቂ ስልጠና ወስደው ወደ ሰራ መግባታቸውንም ገልጿል።

ከሴት ወጣት ተሳታፎዎች ደግሞ ወጣት አፀደ ወንድሙ እንዳለችው ሴቶች ከወንዶች እኩል ወታደራዊ የሙያ ስልጠና ወስደን የከተማችንን ሰላምና ፀጥታ በማስከበር ሥራ ተሰማርተን እየሰራን ነው።

በተለይም የከተማዋ ወጣቶች ከሚሊሻዎችና ፖሊሶች ጋር ሆነው በለሊት ጥበቃና ፍተሻ ላይ በቅንጅት የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት እየሰጡ  መሆናቸውን ተናግራለች።

የአዳማ ከተማ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ወጣት ያደታ አብዲሳ በበኩሉ በከተማዋ አምስት የመግቢያ በሮች ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን 24 ሰዓት እየሰሩ መሆኑን ተናግሯል።

በከተማዋ ከ2 ሺህ 400  በላይ ወጣቶችን በማሳፍ በ28 ቋሚ የፍተሻ ኬላዎችና በ150 ተንቀሳቃሽ የፍተሻ ጣቢያዎች በሶስት ፈረቃ ቀንና ለሊት እየሰሩ ነው ብሏል።

በዚህም በአጠቃላይ በምስራቅ ሸዋ ዞን ውስጥ ከአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተላላኪ ሰርጎገቦች የሰላምና ፀጥታ  ስጋት ከመቀነስ አኳያ አመርቂ ውጤት መገኘቱንም አመልክቷል።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት አክልሉ ታደሰ እና የኦሮሚያ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር አብደላ አናጂ የአዳማ ከተማ ወጣቶችን የለሊት የሰላምና ፀጥታ ስራዎችን ትናንት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ወጣት አክልሉ በዚሁ ጊዜ በተለይም ለኢዜአ እንደገለጸው የጠላትን አፍራሽ ሴራ በማምከን የሀገሪቷን ህልውና ለማስጠበቅ ወጣቶች የላቀ ሚና እየተጫወቱ ናቸው።

በሀገሪቱ ከ1 ነጥቦ 2 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በፈቃደኝነት በለሊት ጥበቃ ስራ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት በመስራት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ ተፈፃሚነት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ አካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ከማድረጋቸውም ባላይ የሽብር ቡድኖችን  እንቅስቃሴ በመቆጣጠር እያከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማ መሆኑን በመስክ መልከታ ተረጋግጧል ብለዋል።

ወጣት አክሊሉ እንዳለው ጠላትን ማሸነፍና ሀገራቸውን ለማሻገር አልመው ቀን ከለሊት በሚሰሩት ወጣቶች ብርታትም አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ከተላላኪዎቻቸው ጋር ያሰቡት ሁሉ የቀን ቅዥት ሆኖባቸዋል።

የኦሮሚያ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር አብደላ አናጂ በበኩሉ በኦሮሚያ በ19 ዋና ዋና ከተሞችና በ21 ዞኖች ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ በንቃት እየተሳፉ ነው ብሏል።

የክልሉ ወጣቶች በራሳቸው ፈቃድ በመደራጀትና ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ ጭምር ለክልሉ ሰላም መከበር በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ መሆኑም አስታውቋል።

በተለይም የአሸባሪዎቹን ሸኔን እና የህወሓት ጁንታን አፍራሽ እንቅስቃሴ ከመግታትና የጠላት አሉባልታን ከማምከን አኳያ ወጣቶቹ የላቀ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።

የክልሉ ወጣቶች በአሸባሪው ህወሓት የተደቀነውን የህልውና ስጋት ለመቀልበስ እየተካሄደ ላለው “ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት” ስኬት እያደረጉ ያለውን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም