የጥቁር ገበያ ምንዛሬ ኢትዮጵያን የማዳከም ዘመቻ አካል መሆኑን መገንዘብ ይገባል

92

ህዳር 26/2014 (ኢዜአ ) የጥቁር ገበያ ምንዛሬ ኢትዮጵያን የማዳከም ዘመቻ አካል በመሆኑ "ህጋዊ የምንዛሬ አማራጮችን ብቻ መጠቀም ይገባል" ሲሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ፤ በህገ-ወጥ መንገድ የሚመነዘር የውጭ አገር ገንዘብ በአመዛኙ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚሰሩ ኃይሎች እንደሚውል ነው የተናገሩት፡፡

ይህም ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ የማዳከም ዘመቻ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ድርጊቱ በሁለት መልኩ አገርን እንደሚጎዳ አብራርተዋል፡፡

በአንድ በኩል ጦርነት ከፍተው አገር እየወጉ የሚገኙ የውስጥ ጠላቶችን አቅም ለማጎልበት የሚውል ሲሆን፤ በሌላ  በኩል  ደግሞ ገንዘብ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገር እንዲሸሽ በማድረግ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት፡፡

በዚህም የውጭ አገር ገንዘብን በጥቁር ገበያ መመንዘር ለጥቂት የገንዘብ ጭማሪ ሲባል አገርን የሚጎዱ ኃይሎችን መተባበር መሆኑን መገንዘብ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ገንዘብን በህጋዊ መንገድ ብቻ በመመንዘር የኢትዮጵያን ህልውና ለመጠበቅ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመቆም የአገራቸውን ህልውና ለመጠበቅ ዋጋ እየከፈሉ ባሉበት በዚህን ወቅት የውጭ አገር ገንዘብ በህጋዊ መንገድ መላክ ከአገር ወዳድ ዜጎች የሚጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ወደ አገር ውስጥ ከሚላከው የውጭ አገር ገንዘብ መካከል በህጋዊ መንገድ የሚመነዘረው ከ30 በመቶ እንደማይበልጥ ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም