በመስኖ የሚለማ መሬት ሁሉ ጥቅም ላይ ይውላል --ዶክተር ይልቃል ከፋለ

143

ባህር ዳር ህዳር 26/2014 (ኢዜአ ) በጦርነቱ ምክንያት የታጣውን የሰብል ምርት ለማካካስ በበጋው ወቅት በመስኖ መልማት የሚችል መሬት ሁሉ ጥቅም ላይ ይውላል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።
በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች  በበጋ  መስኖ ስንዴ ልማት ዙሪያ ዛሬ በባህርዳር መክረዋል ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በምክክር መድረኩ ላይ እንዳስታወቁት  ሀገር ለማፍረስ በተነሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶች በተከፈተው ጦርነት ምክንያት በኢኮኖሚው ላይ እያጋጠመ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመቋቋም በግብርና ዘርፍ በትኩረት መስራት ይገባል።

"በክልሉ ብሎም በሃገሪቱ  በተጋረጠው የህልውና አደጋ ምክንያት ከዜጎች ሰብአዊ ጉዳት ባሻገር የምርት መቀነስ ተከስቷል" ብለዋል።

በመኽር እርሻ ወቅት ያጋጠመውን የምርት መቀነስ ለማካካስና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ለመስኖ ልማት የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በክልሉ በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት ቢኖርም በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ አለመዋሉን ጠቁመዋል ።

"በተለይም በጦርነቱ ምክንያት ያጋጠመውን የሰብል ምርት መቀነስ ለማካካስ በዘንድሮ በጋ ወቅት በመስኖ መልማት የሚችል መሬት ሁሉ  ጥቅም ላይ ይውላል" ብለዋል ።

መሬቱ ኑሯቸው ማልማት የማይችሉ ግለሰቦች መሬታቸው በጊዜያዊነት ማልማት ለሚችሉ ባለሃብቶች ተላልፎ እንደሚሰጥ  አስታውቀዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የገጠር መሬት አስተዳደርና ግብርና ተቋማት ለአፈጻጸሙ ስከኬታማነት  በትጋት እንዲሰሩ አስገንዝበዋል ።

የክልሉ መንግስት የቆላ ስንዴም ሆነ ሌሎች ሰብሎች በመስኖ እንዲለሙ  በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

"በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች በየደረጃው የሚገጥሟቸው ችግሮች ፈጥነው ይፈታሉ" ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ "የክልሉ መንግስት ችግሮችን ተከታትሎ ለመቅረፍ ቁርጠኛ ነው" ሲሉ አረጋግጠዋል።

"በተለይም አርሶ አደሮች የውሀ አማራጮችን ተጠቅመው በመስኖ ልማቱ በትኩረት ከሰሩ ግንባር ላይ እንደሚፋለመው ሰራዊት ሁሉ ለሃገራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ ይቆጠራል" ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የመስኖ ልማትን ትኩረት ሰጥተው በፍጥነት ወደ ልማት በመግባት የህብረተሰቡን ኑሮ ለመለወጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በምክክር መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም