አገር ለማፍረስ ከታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር በባንዳነት ተሰልፎ እየወጋን ያለውን አሸባሪው ህወሓትን እናወግዛለን

232

ህዳር 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር በባንዳነት ተሰልፎ እየወጋን ያለውን አሸባሪው ህወሓትን እናወግዛለን ሲሉ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች ገለጹ።

የክልሉ ተወላጆች የአሸባሪው ህወሓትን ድርጊት የሚቃወም በአዲስ አበባ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ሰላማዊ ሰልፍ እያደረጉ ይገኛሉ።

ሰልፈኞቹ የትግራይ ህዝብ ጠንቅ የሆነውን አሸባሪው ህወሓትን ለማውገዝና ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መሆናቸውን ለመግለጽ መውጣታቸውን በሚያሰሙት መፈክር እየገለጹ ይገኛሉ።

“የትግራይ ህዝብ ለጥቂት ሰልጣን ጥመኞች ሲባል ማለቅ እንደሌለበት እና በክልሉ ያሉ ህዝባችንን መንግስት ከአፈና እና ጭቆና ነጻ ያውጣልን” ሲሉ ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።

“የትግራይ ህዝብ ከህወሓት በፊት የነበረና በኋላም የሚኖር መሆኑን የገለጹት ሰልፈኞቹ፤ የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ አይደሉም፤ ሊሆኑም አይችሉም” ብለዋል።

“ተጋሩ ሀገር የመግንባት እንጂ ሀገር የማፍረስ ታሪክ እንደሌለው የገለጹት ሰልፈኞቹ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር በባንዳነት ተሰልፎ እየወጋን ያለውን አሸባሪው ህወሓት እናወግዛለን” ሲሉ በያዙት መፈክር ገልጸዋል።

ሰልፈኞቹ “የትግራይ ህዝብ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነው፤ አሸባሪው ህወሓት ግን የትግራይ ጠላት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ሰልፈኞቹ የምዕራብዊያን ጣልቃ ገብነትን በማውገዝ የ”በቃ” ‘#Nomore’ ንቅናቄ መፈክሮችን አሰምተዋል።