የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላም ከጥፋት ተላላኪዎች በመጠበቅ የጸጥታ አስከባሪውን እየደገፉ ነው

89

አሶሳ፣ ህዳር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአካባቢያቸውን ሰላም ከአሸባሪው የህወሃት ቡድን ርዝራዥ ተላላኪዎች ጥፋት ነቅተው በመጠበቅ የጸጥታ አስከባሪ ሃይሎችን እየደገፉ መሆናቸውን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በምሽት አካባቢያቸውን በመጠበቅ ላይ የሚገኙ የከተመዋ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤  የአካባቢአቸውን ሠላም ከጸጥታ ሃይሎች ጎን በመቆም ነቅተው እየጠበቁ ነው፡፡

በምሽትም ሆነ በቀን የተጠናከረ ፍተሻ በማድረግ በርካታ ከአሸባሪዎቹ ህወሃትና  ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የጠረጠሯቸውን ግለሰቦች ለጸጥታ ሃይሉ ማስረከባቸውን ነው ያመለከቱት፡፡

በተለይም አጠራጣሪ ጉዳዮችን አስመልክቶ ፈጥነው መረጃዎችን ለጸጥታ ሃይሎች በመስጠት ለከተማው መረጋጋት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አሶሳ አስተማማኝ ሠላም እንዳላት አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

ሠራዊቱን በግንባር ተገኝተው በመምራት የጠላትን የጥፋት ተልዕኮ እያመከኑ  የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከአፍሪካ አልፎ ለመላው ዓለም አርአያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈለግ በመከተል የአሶሳን ሠላም ለማስቀጠል በቀን እና በማታ ጥበቃ በማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረጉ እንደሚገኙም አመልክተዋል።

አባቶች ኢትዮጵያን ለማዳን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሀገራትን ሠላም ለማስጠበቅ ጭምር መዝመታቸውን አስታውሰው፤ የአሁኑ ትውልድም አገሩን ለማዳን ዝግጁ እንደሆነ መታወቅ እንዳለበት ጠቅሰዋል።

በሐሰተኛና በተዛባ ዘገባ ኢትዮጵያን ማሸነፍ እንደማይቻል ተናግረው፤ ምዕራባዊያን ካልተገባ ድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የቡድኑ የጥፋት ተልዕኮ ለማክሸፍ ከጠቅላይ ሚኒስትር እስከ ክልል አመራር ሲዘምት አካባቢውን ሳይጠብቅ ቤቱ የሚቀመጥ ነዋሪ እንደማይኖርም ገልጸዋል።

የአሸባሪውን የጥፋት ድርጊት ለማስቆም እየተካሄደ ባለው ተጋድሎ በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ እንደሆኑም አረጋግጠዋል፡፡

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ አባልና የፖሊስ መምሪያ ሃላፊ  ኮማንደር ቡሽራ አልቀሪብ፤ በተለይ አዋጁ ከተደነገገ በኋላ ህብረተሰቡ የአካባቢው ሠላም ለማስጠበቅ  የሚያደርገው ጥረት መጨመሩን ይናገራሉ፡፡

ይህም ለጸጥታ አስከባሪ ሃይሎች ተጨማሪ አቅም እንደፈጠረ ነው ያመለከቱት፡፡

እንዲሁም የሃገር መከላከያ ሠራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ እና ሌሎችም የከተማውን ህብረተሰብ ያሳተፈ ቅንጅታዊ አሰራር እየተከተሉ ነው ብለዋል፡፡

አዋጁን መሠረት በማድረግ ለአሸባሪው ቡድን ቀጥተኛ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ፣ የስልክ ልውውጥ የነበራቸው እና በማህበራዊ የትስስር ገፆች ሀሰተኛ መረጃ ሲለቁ የተደረሰባቸው ግለሰቦች  በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አብዛኞቹ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ኮማንደር ቡሽራ አስረድተዋል፡፡

ሠላም እና ደህንነት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ ሳይሆን ተከታታይነት ያለው  ክትትል የሚያስፈልገው ጉዳይ እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ የኮሚቴው አባልና የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልሙኒዬም አብዱልዋሂድ ናቸው፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች  ለሃገር መከላከያ ሠራዊት ደረቅ ስንቅ እያዘጋጁና ደም እየለገሱ የደጀንነት ድጋፋቸውን እንደቀጠሉ ገልጸዋል።

በርካታ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉንመ ጠቁመዋል፡፡

አሶሳ የተረጋጋች ትሁን እንጂ የአሸባሪው ህወሃት ርዝራዥ ተላላኪዎች የሉም ማለት አይቻልም ያሉት ከንቲባው፤ ህብረተሰቡ በሚሰጠን ጥቆማ የነዋሪው ደህንነት የማስጠበቁ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም