በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች አሸባሪው ህወሓትን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ያደርጋሉ

250

ህዳር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች አሸባሪው ህወሓትን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በነገው ዕለት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ እንደሚያደርጉ ተገለጸ።

ሰልፉን አስመልክቶ የክልሉ ተወላጅ የሆኑ የአገር ሽማግሌዎችና የሰልፉ አዘጋጆች ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በሰልፉ በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ለትግራይ ህዝብ ጠንቅ የሆነውን የህወሓት አሸባሪ ቡድን ለማውገዝ እና ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን መሆናቸውን ለመግለጽ የሚደረግ እንደሆነ ተገልጿል።

ከአዘጋጆቹ መካከል የሰላም አምባሳደር ምዑዝ ገብረህይወት እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሓት እታገልለታለው በሚለው በትግራይ ሕዝብ ስም ላለፉት ዓመታት ሲነግድ፣ ሲዘርፍ፣ ሲያስርና ሲያሳድድ ከመኖሩ ባሻገር ህዝቡ በድህነት እንዲማቅቅ ምክንያት ሆኗል።

የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ፣ ኢትዮጵያን ከጥፋት የሚከላከል፣ የሚጠብቅ፣ ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር የተሳሰረና የተጋመደ እንዲሁም አብሮ የኖረ በመሆኑ ይህ አሸባሪ ቡድን የትግራይን ህዝብ ፍጹም አይወክልም ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም የሽብር ቡድኑ እኩይ ዓላማ በአጭር እንዲቀጭና ህዝቡም ወደቀድሞ ሰላሙ እንዲመለስ የክልሉ ተወላጅ የሆነ በሙሉ የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ የሽብር ቡድን በርካታ የትግራይ ወጣቶችን ለሞት ዳርጓል፤ የህጻናትን፣ እናቶችና አባቶችንም ህይወት የነጠቀ አፍራሽ ኃይል መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

ለአገርም ሆነ ለህዝብ ግድ ለሌለው ለዚህ አጥፊ ቡድን ወጣቱ መሞት እንደሌለበት አውቆ በመንግስት የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ እጁን እንዲሰጥም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አቶ ተስፋይ አለማየሁ በበኩላቸው፤ ህዝቡ ሞትና እልቂት ይብቃ! በማለት ቅድሚያ ለአገር በመስጠት ከመንግሥት እና ከአገር መከላከያ ጎን መሰለፍ አለበት ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አሜሪካና ሌሎችም ምዕራባዊያን አገራት ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና በመቃወም እና በማውገዝ ለአገሩ ሰላምና አንድነት መምጣት የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ እንጂ ተገንጣይ እና አሸባሪ እንዳልሆነ እያወቁ በጠመንጃ ተገደው ወደ ጦርነት የገቡ የትግራይ ወጣቶች እጃቸውን ለመከላከያ ሠራዊቱ እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።