እንደ ሃገር የገጠመንን ፈተና ለማለፍ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህላችንን ማሳደግ አለብን

103

ደብረ ብርሃን፤ ህዳር 25/2014 (ኢዜአ) እንደ ሃገር የገጠመንን የህልውና ፈተና በአሸናፊነት ለማለፍ የአባቶቻችንን ዘመን ተሻጋሪ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህላችንን ማሳደግ አለብን ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አመለከቱ።

የጤና ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴሮች እንዲሁም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በአሸባሪው የህወሃት ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለጤና ተቋማት ከ37 ሚሊየን ብር በላይ  የሚገመቱ ቁሶች ድጋፍ  አድርገዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ  ዛሬ በተከናወነው የድጋፍ ርክክብ ወቅት ዶክተር ሊያ ታደሰ  እንዳሉት፤በአማራና አፋር ክልሎች በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ከመፈናቀላቸውም በላይ የህዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

 እንደ ሀገር የገጠመንን ከበድ ፈተና ለማለፍ  የአባቶቻችንን ዘመን ተሻጋሪ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህላችንን  ማሳደግ አለብን ነው ያሉት።

አሁን ላይ በርካታ የስራ ጫና ያለባቸው የደብረ ብርሀን አጠቃላይ ሆስፒታልና ሌሎች የጤና ተቋማት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ በቁሳቁስ መደገፍ ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ለደብረ ብርሀን አጠቃላይ ሆስፒታልና ለሃኪም ግዛው መታሰቢያ ቲችንግ ሆስፒታል  ‘’ሰርት’’ ከተባለ አለም አቀፍ ድርጅትና ከጤና ሚኒስቴር 25 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገባቸው አንድ ሺህ 900 ዓይነት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።

እንዲሁም የሚኒስቴሩ ሰራተኞች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት አልባሳትና የምግብ ድጋፍ ማመቻቸታቸውን ዶክተር ሊያ ጠቅሰዋል።

ለህክምና ተቋማቱም ሆነ ለተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ  ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ  በበኩላቸው፤ አሸባሪው  አማራጭ የፖለቲካ ሀሳብ አቅርቦ በሀገራዊ ልማት ላይ መሳተፍ ሲሳነው ሀገር ለማፍረስ  ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል።

በሽብር ቡድኑ ተፈናቅለው በመጠለያ ላሉ ወገኖች አምስት ዩኒቨርሲቲዎችን በማስተባበር ከ6 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና አልባሳት ድጋፍ ማምጣታቸውን ገልጸዋል።

ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋምና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ስራ ለማስጀመር  በውጭና ሀገር  ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ተፈናቃዮች ወቅታዊ ችግራቸውን ለማቃለል እንዲያግዛቸው  3 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶችን ድጋፍ ማመቻቸታቸውን የገለፁት ደግሞ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ ናቸው።

ምክር ቤቱ ባሉት ሙያተኞች ጥናትና ምርምር በማድረግ በቀጣይ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ከመንግስት ጋር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱል ከሪም መንግስቱ ፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን  በወረራቸው የክልሉ አካባቢዎች 40 ሆስፒታሎች፣ 2 ሺህ 253 ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች፣ አራት የደም ባንኮችና አንድ የኦክስጅን ሴንተርን ሙሉ በሙሉ አውድሟል ብለዋል።

ዛሬ ለጤና ተቋማት የተደረገው ድጋፍ  ችግሩን  ለመፍታት የሚያግዝ መሆኑን ገልፀው፤ በቀጣይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች በጋራ እንዲረባረቡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን  ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ወልደ አማኑኤል፤ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይም ተፈናቃዮችን መልሶ ለማደራጀት በሚደረገው ጥረት የሁሉም እገዛ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም