በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

218

ጋምቤላ፤ ህዳር 25/2014 (ኢዜአ)…በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አስገነዘቡ።

‘‘በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት ይቁም ’’ በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም የፀረ- ፆታዊ ጥቃት ቀን በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በልጆች፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በሀገር ደረጃም የሚያደርሰውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም አሁን ላይ የህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው የአፋርና የአማራ ክልሎች በሴቶችና ህፃናት ላይ አረመኔያዊ ድርጊቶችን መፈጸሙን ገልጸዋል።  

እንደ ጋምቤላ ክልል በተለያዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱት ፆታዊ ጥቃቶች ቀላል አይደሉም ብለዋል።

በመሆኑም በሰላም እጦትና በተለያዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ማህበራዊ ኃላፊነታችውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዘንድሮው  ዓለም አቀፍ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን ከህዳር 16 ቀን 2014 ጀምሮ ለሁለት ሳምንት የሚከበረው የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የአጋርነት ሚናቸውን ለማጠናከር ያለመ ነውም ብለዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር በዓሉን የህወሓት የሽብር ቡድን በከፈተው ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍና መንከባከብ እያከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የመከላከሉ ስራ በሴቶች መዋቅርና አደረጃጀት ብቻ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል።

በመሆኑም በሴቶችና ህፃናት የሚደርሱ ጥቃቶች በመከላከል የማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነታቸው ለማረጋገጥ ሁሉም በጋራና በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግስት በተለይም በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ በጋብቻ ላይ ጋብቻ፣ ያለ እድሜ ጋብቻ ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ለስኬታማነቱ ሁሉም ሊተባበር ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ቾል ቶንግይክ እንዳሉት በክልሉ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት ማስቆም የሁሉንም ማህበረሰብ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው።

በዓለም 30ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው የዓለም አቀፍ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን በጋምቤላ ክልል በፓናል ውይይት፣ በተማሪዎች የእግር ጉዞና ሌሎች ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።