የክልሉን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ ነው

78

ጋምቤላ፣ ህዳር 25/2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የሰላምና ፀጥታ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

በጋምቤላ ክልል ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወኑ ያሉ የሰላምና የፀጥታ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ የፀጥታ ዘርፉን በሰው ኃይል የማደራጀትና የማጠናከር ስራ እየተከናወነ ነው።

የህወሓት የሽብር ቡድንና ተላላኪዎቹ የደቀኑትን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ በአጠረ ጊዜ በድል ለመቀልበስ እየተካሄደ ላለው "ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" ስኬት የፀጥታ ዘርፉን የማጠናከር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የክልሉ ሕዝብ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ በየደረጃው ካለው አመራርና የፀጥታ ሀይል ጋር በቅንጅት በመስራቱ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም እራሱን ጋነግ ብሎ የሚጠራው የአሸባሪዎቹ የህወሓትና ሸኔ ቡድኖች ተላላኪ የክልሉን ሰላም ለማወክ የሚያደርገው ሙከራ በክልሉ የፀጥታ ኃይሉ መክኗል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ክልሉ ሰፊ የድንበር ወሰን ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርንና ሙርሌ በተሰኘ ጎሳ አልፎ አልፎ የሚያጋጥመውን የፀጥታ ችግር ለመከላከልም እየተሰራ ነው።

የጋምቤላ ክልል ሕዝብ በተለይም አሸባሪው ህወሓት የደቀነውን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ እየተካሄደ ያለው "ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" በአጠረ ጊዜ በድል እንዲጠናቀቅ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በተለይም የህወሓትና የሸኔ አሸባሪ ቡድኖችን ሀገር የማፍረስ እኩይ ተልዕኮ ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት የክልሉ ወጣቶች በራሳቸው ፈቃድ ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም