አፍሪካ ከምዕራባውያኑ ተፅዕኖ ለመውጣት የዘላቂና ጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆን አለባት

55

ህዳር 25/2014/ኢዜአ/ አፍሪካ ከምዕራባውያኑ ተፅዕኖ ለመውጣት የዘላቂና ጠንካራ የኢኮኖሚ ባለቤት መሆን አለባት ሲሉ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት አምራቾች ገለፁ።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 12ኛው የኦል አፍሪካ ሌዘር ሾው ዐውደ ርዕይ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት አምራቾች ተሳትፈዋል።

ከኡጋንዳ የመጡት አላን ኒንሲማ፤ "ራዳ ሹዝ" የተሰኘ ድርጅት የወከሉ የተለያዩ ጫማዎችና ቀበቶዎችን ይዘው ቀርበዋል።

አዲስ አበባ ፍፁም ሰላም ናት፤ አውደ ርእዩም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በአፍሪካ የንግድ ትስስሩንና የኢኮኖሚ ትብብሩን በማጠናከር ለጋራ ልማትና እድገት ለመስራት ስለሚያስፈልግ እንዲህ አይነት ግብይቶች ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አፍሪካ ከምዕራባውያኑ ተፅዕኖ ለመውጣት የዘላቂና ጠንካራ የኢኮኖሚ ባለቤት መሆን እንዳለባትም ተናግረዋል።

ከሱዳን ስማልታ ጄንዩን የቆዳ ውጤቶች አምራች የመጡት ረሺድ አቡበከር በበኩላቸው፤ ኢትዮያጵዊያን አንድነታቸውን ለማጠናከርና እድገታቸውን ለማፋጠን የሚተጉበት ወቅት መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

አፍሪካዊያን ለጋራ ልማትና እድገት በትብብር የሚሰሩበት ጊዜ አሁን መሆኑን በመጥቀስ አህጉሩ ከጫና የሚወጣበት ብቸኛው መንገድ አብሮ መልማት ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በአፍሪካ በተለይም የቆዳ ኢንዱስትሪ ገበያው እያደገ በመምጣቱ ለእድገት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አህጉሪቷን ከምዕራባውያን የኢኮኖሚ ጥገኝነት ለማላቀቅ መሰል የኢንዱስትሪ ልማቶችን ማስፋፋት ይገባልም ነው ያሉት።

አፍሪካ ያላትን ሀብት ተጠቅማ እንድታድግ ጠንካራ የስራ ባህልን ማዳበር እንዲሁም ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም