"የጸጥታ ሃይሉ በአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ላይ እየወሰደ ያለው የተቀናጀ እርምጃ አቅማቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እያዳከመው ነው"

78

ህዳር 25/2014 /ኢዜአ /የጸጥታ ሃይሉ በአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ላይ እየወሰደ ያለው የተቀናጀ እርምጃ የቡድኖቹን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እያዳከመ መሆኑ ተገለጸ።

ሕብረተሰቡ አሸባሪ ቡድኖቹን እስከ መጨረሻው ለመቅበር በሚደረገው ጥረት የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ አንዲቀጥልም ጥሪ ቀርቧል።


የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነሮች አስቸኳይ ልዩ ጉባኤ 'ዘመቻ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት' በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በጉባኤው ላይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤልና ሌሎች የኮሚሽኑ አመራሮች እንዲሁም የክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ተገኝተዋል።

በጉባኤው ላይ  በጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) መሪነት እየተካሄደ ባለው የህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ የተገኙ ድሎች፣ አፈጻጸምና በቀጣይ ዘመቻውን ወደላቀ ደረጃ ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ዉይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የፌደራልና የክልል የጸጥታ አካላት በአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ቡድኖች ላይ እየወሰዱ ባለው የተቀናጀ እርምጃ አሸባሪ ቡድኖቹ አቅማቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተቀናጀ እርምጃው አኩሪ ድሎች መመዝገባችውንና ሁለቱም አሸባሪ ቡድኖች ስጋት ከመሆን ወርደው በየቦታው መበታተናቸውን ተናግረዋል።

የተበታተነውን ሃይል የማጽዳት ስራ በጸጥታ ሃይሉ እየተከናወነ እንደሚገኝና ከዚህም ጎን ለጎን ከአሸባሪዎቹ ነጻ በወጡ አካባቢዎች ዜጎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በቀጣይ የተመታውና የተበታተነው የጠላት ሃይል በየከተማው ሰርጎ ገቦችን በማስገባት ሽብር ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት በተቀናጀ መልኩ የማክሸፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

በየአካባቢው የሚደረጉ የፍተሻዎችና የጸጥታ ስምሪቶችን ይበልጥ በማጠናከር የጠላትን እኩይ አላማ ሕልም የማድረግና የተበተኑትን የማጽዳት ስራዎች ይከናወናሉ ነው ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ።

ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን በዘላቂነት ለመግታት ችግሩን ከምንጩ የማድረቅ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚከናወንም አስረድተዋል።

ሕብረተሰቡ አሸባሪ ቡድኖቹን እስከ መጨረው ለመቅበር በሚደረገው ጥረት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽነር ጀነራሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የክልልና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች በበኩላቸው የጸጥታ ሃይሉ በአሸባሪዎቹ የሕወሓትና የሸኔ ቡድኖች ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደረስባቸው አድርጓል ብለዋል።

በአማራ ክልል የጸጥታ መዋቅሩ ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየወሰደ ባለው እርምጃ ጠላትን እየደመሰሰና አካባቢውን እያጸዳ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በአፋር ክልል አሸባሪው ሕወሓት ሚሌን በመያዝ የኢትዮ-ጅቡቲ መስመርን የመያዝ ሀሳቡ ሕልም ሆኖ እንደቀረና ምሽጎቹን በመሰባበር እንዲንኮታኮት በመደረጉ ክልሉ ሰላማዊ ሁኔታ ላይ አንዳለ ተጠቁሟል።

በኦሮሚያ ክልልም አሸባሪው ሸኔ ላይ በጸጥታ ሃይሉ እየተወሰደ ባለው እርምጃ የደነቀነውን ስጋት በመቀልበስ አቅሙ እንዲዳከም መደረጉ ነው የተገለጸው።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል፣ በድንበር ሰርጎ በመግባት ጥቃት ለማድረስ የሚፈልጉ ተላላኪ ሃይሎችን በመደምስስ ስኬታማ ስራ መከናወኑ ተገልጿል።

አዲስ አበባም በጸጥታ አካላትና ሕብረተሰቡ ቅንጅት እየተከናወነ ባለው ስራ ከተማዋ ፍጹም ሰላማዊ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝም ተጠቁሟል።

ሕብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ሆኖ የሚያከናውነውን ስራ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ኮሚሽነሮቹ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነሮች አስቸኳይ ልዩ ጉባኤ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮቹ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጸጥታ አካላት የግዳጅ አፈጻጸም  አስመልክቶ ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጓል።

በተጨማሪም በጉባኤው ላይ በ'ዘመቻ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት' የፖሊስ ሃይሉ በቀጣይ በሚኖረው የግዳጅ አፈጻጸም ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች መሰጠታቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም