በአማራ ክልል ለህልውና ዘመቻው በጥሬ ገንዘብ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል

70

ባህርዳር፣ ህዳር 25/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ለህልውና ዘመቻው ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የክልሉ የጥሬ ገንዘብ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታወቀ።

የኮሚቴው ሰብሳቢና የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ አማረ ሰጤ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አሸባሪው ህወሃት የፈፀመውን ወረራ ለመመከት እየተካሄደ ላለው የህልውና ዘመቻ በተጀመረው ሃብት ማሰባሰብ አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው ።

ክልሉ በከፈተው የገቢ ማሰባሰቢያ የባንክ ሂሳብ ቁጥር  በጥሬ ገንዘብ ከ1 ቢሊዮን 858 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ ለህልውና ዘመቻው ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።

የገንዘብ ድጋፉ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከመንግስት ሰራተኛው የወር ደመወዝ፣ ከባለሃብቶች፣ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ከልማት ድርጅቶችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰበ መሆኑን አመልክተዋል።

ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 35 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብሩ በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን  ድጋፍ የተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በገንዘብ ከተሰበሰበው በተጨማሪ  በአይነት የተደረገው ድጋፍም አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

በስንቅ ዝግጅት 60 ሺህ 325 ኩንታል በሶ፣ ድርቆሽ፣ ቆሎ፣ ሽሮና ቴምር እንዲሁም 1ሺህ 528 ኩንታል ስኳር፣ 56 ሺህ 836 ካርቶን ብስኩትና 178 ሺህ ደርዘን እሽግ ውሃና ጭማቂ  ተሰብስቦ በግንባር ለሚገኘው የፀጥታ ሃይል መላኩን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከ10 ሺህ በላይ ሰንጋዎች እንዲሁም በግና ፍየል ወደ ግንባር ለመላክ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ህብረተሰቡና ሌሎች አካላት የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል ።

በአማራ ክልል ህወሀት በፈጸመው ወረራ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚበልጡ ወገኖች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን  አቶ አማረ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም