የትግራይ ሕዝብም በአሸባሪው ህወሓት ተጠቂ በመሆኑ ከመንግሥት ጎን ቆመን እንታገለዋለን

78

ህዳር 25/2014/ኢዜአ/ የትግራይ ሕዝብ እንደሌላው ሕዝብ ሁሉ በአሸባሪው ህወሓት ተጠቂ በመሆኑ ከመንግሥት ጎን በመቆም እንታገለዋለን ሲሉ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ዛሬ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ባካሄዱት ውይይት፤ የትግራይ ሕዝብ ለ27 ዓመታት በአንድ ገዥ ፓርቲ ታፍኖ ቁም ስቅሉን ሲያይ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮም በአሸባሪው ህወሓት ለአፈናና ለአላስፈላጊ ጦርነት ተዳርጓል ብለዋል።

ጦርነቱን የሚያካሂደውና አገር ለማፍረስ የተነሳው የአንድ አካባቢ ቡድን ነው ያሉት አቶ አማኑኤል ኪሮስ  የሽብር ቡድኑ የትግራይ ሕዝብ ውክልና የሌለውና ለጥቂቶች ጥቅም የቆመ መሆኑ እንደሚታወቅ ገልጸዋል።

ከአሸባሪ ቡድኑ ጋር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተባባሪ የሆኑ አካላት ድርጊታቸው የተሳሳተ መሆኑን በመረዳት መንግሥት ባቀረበው ጥሪ ተጠቅመው እጃቸውን ለመከላከያ ሠራዊት በመስጠት ወደ ሠላማዊ ኑሮ እንዲቀላቀሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተለይም በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ይህን ሽብርተኛ ቡድን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

፤ የትግራይ እናቶች እየተገደዱና እየተነጠቁ ልጆቻቸውን ላልተፈለገ ጦርነት እየማገዱ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ መሰሉ ረዳ ናቸው።

የጥቂት ቡድኖችን ጥቅም ለማስከበር የትግራይ ሕዝብና እናቶች የልጆቻቸውን ሕይወት መስዋዕት ማድረግ የለባቸውም ያሉት ወይዘሮ መሰሉ አሸባሪው ህወሓት በቃህ ሊባል ይገባል ነው ያሉት፡፡

ህጻናትን ተንከባክቦ ማሳደግ ሲገባ የትግራይ ህጻናትን ላልተገባ መስዋዕትነት የሚያቀርበውን ሽብርተኛ ቡድን መቃወምና መታገል እንደሚያስፈልግ፤ ቡድኑ ፀረ-ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ፀረ-ትግራይ መሆኑን ሁሉም መረዳት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለስ ሸጋው፤ ሽብርተኛው ህወሓት የጥቂት አጥፊና ወንጀለኞች ቡድን ከመሆኑ በቀር በምንም መንገድ የትግራይን ሕዝብ የማይወክል ነው ብለዋል።

ይህን የትግራይን ሕዝብ ለመከራ የዳረገ ወንጀለኛ ቡድን ለማጥፋት በሚደረገው ዘመቻ የትግራይ ተወላጆች ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ሽብርተኛው ቡድን በግንባር ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ባልተናነሰ በሐሰት ፕሮፓጋንዳና ሰርጎ ገቦችን በማሰማራት የያዘውን ዕቅድ ለማክሸፍ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋሉ ስራ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል።

ተጠርጣሪዎችን በመለየቱ ተግባር ንጹሃን ከተያዙ በፍጥነት እየተጣራ የመልቀቅ ሥራ እንደሚከናወን ጠቅሰው፤ የትግራይ ተወላጆችም በዚህ የማጥራት ሥራ በመሳተፍ አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም