ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ለአፋር ክልል ድጋፍ እንዲያደርጉ በአዲስ አበባ ከተማ በሚኖሩ የአፋር ተወላጆች እና ወዳጆች የተቋቋመ ግብረኃይል ጠየቀ

64

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል ባደረሰው ቀውስ ሳቢያ ለችግር ለተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉ በአዲስ አበባ ከተማ በሚኖሩ የአፋር ተወላጆች እና ወዳጆች የተቋቋመ ግብረኃይል ጠየቀ።ግብረኃይሉ በክልል ጉዳት ለደረሰበት ህዝብ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል፡፡


የግብረኃይሉ ሰብሳቢ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ የሆኑት ዘሃራ ኡመድ በመግለጫው እንዳስታወቁት፤ አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል በሚገኙ አካባቢዎች በሰውና በንብረት ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት አድርሷል፡፡


በአፋር ክልል በጥቅምት ወር መጀመሪያ በተደረገው ዳሰሳ ጥናት መሰረት ህወሓት በፈፀመው ወረራ ከ360 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ21 ወረዳዎች መፈናቀላቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ የክልሉ መሰረተ ልማቶች ላይ አሸባሪው ኃይል ውድመት ማስከተሉን ነው የገለጹት፡፡


የክልሉ ህዝብ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጥሯዊ ቀውሶች አማካኝነት ለችግር የተጋለጠበት ሁኔታ እንደነበር ገልፀው፤ አሸባሪው ኃይል ያደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ሲታከልበት ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል ሲሉ አፈ-ጉባኤዋ ገልጸዋል፡፡


አያይዘውም አጠቃላይ በክልሉ በአሁኑ ወቅት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የኢትዮጵያዊያንን እገዛ የሚሹ በመሆኑ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


ግብረኃይሉ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ዜጎች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው ሂሳብ ቁጥር 1000444559512 እገዛ ማድረግ እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም አካል በአዲስ አበባ ከተማ "አዋሬ" በሚገኘው ሱልጣን አሊ ሚራህ መስጂድ በመሄድ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም