የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ኢትዮጵያን በቆዳው ዘርፍ ውጤታማ እንድትሆን ያስችላታል

62

ህዳር 25/2014/ኢዜአ/ የአፍሪካ ነፃ አኅጉራዊ የንግድ ቀጠና ኢትዮጵያ በቆዳው ዘርፍ ያላትን አቅም ተጠቅማ ውጤታማ እንድትሆን እንደሚያስችላት በአፍሪካ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንስቲትዩት ገለፀ።

የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር አማካሪ ፕሮፌሰር መኮንን ኃይለማርያም እንደሚሉት ኢንስቲትዩቱ የአፍሪካ አገራት በጋራ ያቋቋሙት ሲሆን ለዘርፉ እድገት እገዛ የሚያደርግ ነው።

አፍሪካ ከአለም አንድ አራተኛውን የእንስሳት ሀብት የያዘች መሆኗን ገልፀው የቆዳው ዘርፍ አመታዊ የንግድ መጠን 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነም ተናግረዋል።  

አህጉሪቱ ካላት የእንስሳት ሀብት ጋር ሲነፃፀር የምታገኘው ገቢ ያላትን እምቅ ሃብት የሚመጥን እንዳልሆነ በመግለጽ።

ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ወደ ውጭ የሚላኩት ምርቶች እሴት ያልተጨመረባቸው በመሆናቸው ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የቆዳ ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው እንዲላኩ ለማድረግ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በገበያ ትስስርና በልምድ ልውውጥ የአፍሪካ አገራት ዘርፉን እንዲያሳድጉ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

አህጉሪቱ በአመት 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቆዳ ከውጭ የምታስገባ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የአፍሪካ ሀገራት የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጣቸው 10 በመቶ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ልውውጡን  እርስ በእርሳቸው ማድረግ ቢችሉ፤ 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት እንደሚያስችላቸውም አስረድተዋል።

የገበያ ፍላጎቱም ሆነ ጥሬ እቃው በበቂ ሁኔታ በአህጉሪቱ መኖሩን በመጠቆም።

በአህጉሪቱ ያለው ህዝብ በአመት በአማካይ አንድ ጫማ ይገዛል፤ይህ ካለው የሕዝብ ብዛት አንፃር 1 ቢሊዮን ጥንድ ጫማ የሚያስፈልግ ቢሆንም የሚመረተው ግን 200 ሚሊዮን በመሆኑ ቀሪው ከውጭ የሚገባ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አቅም ስላላት በአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ወደ ገበያው ገብታ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ኢንስቲትዩቱ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ኢትዮጵያ በትክክለኛ የንግድ መስመር ግብይት እንድታካሂድና በቆዳው ዘርፍ ተጠቃሚነቷን እንድታሳድግ ያስችላታልም ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የቆዳ አምራቾች በቴክኖሎጂ የተደገፈ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት እንዲፈፅሙ እገዛ ቢደረግና  በአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና በአግባቡ ተጠቃሚ ብትሆን በአግዋ የምታጣውን ገቢ ለመተካት ያስችላልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት  ሌሎች የገበያ አማራጮችን መፍጠር አለባት ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ፀሀፊ አቶ ዳንኤል ጌታቸው ናቸው።

አንደኛው የገበያ አማራጭ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት መሆኑን በመግለፅ።

የአፍሪካ ገበያም እስካሁን ያልታየና በደንብ ያልተጠቀምነው፤ነገር ግን ሊታይ የሚገባ ነው ሲሉም ነው የገለጹት።

1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ህዝብ ያለበትን የአፍሪካ ገበያ ትተን 300ና 400ሚሊዮን ህዝብ ያለበትን ገበያ እንድናይ ሲደረግ ነበር ያሉት አቶ ዳንኤል የአፍሪካ ገበያ አዋጭ እንዳልሆነ ሲነገር የነበረው የሀሰት ትርክትና አሻጥር ነበረም ብለዋል።

በአሸባሪው የተከፈተው ጦርነት ከጦር ሜዳ ባለፈ ውጊያው በሚዲያ የታገዘና ኢኮኖሚን ማዳከምን ያካተተ መሆኑን በመረዳት በሁሉም አውደግንባር መዋጋት አለብንም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም