“ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በታላላቅ ድሎች ታጅቦ እየተካሄደ ነው

68

አዲስ አበባ፣  ህዳር 25/2014 (ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሚመራው “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በታላላቅ ድሎች ታጅቦ እየተከናወነ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በታላላቅ ስኬትና ድሎች ታጅቦ እንደቀጠለ ነው፡፡

ለዘመቻው ዜጎች  ሁለንተናዊ  ድጋፍ እያሳዩ መሆናቸውን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ እስከ ግንባር ድረስ በመዝመትም ታላላቅ ድሎች እንዲመዘገቡ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ የውጪ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የህልውና ዘመቻ በተመለከተ የተለመደ የሀሰት መረጃዎቻቸውን በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም መንግሥት ለትግራይ ክልል እያሰራጨ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ጎን ትተው ድጋፍ እንደሌለ የሚዘግቡበት መንገድ አንዱ ማሳያ ነውም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም አሸባሪው ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ የአፋርና የአማራ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች  ሰብዓዊ ድጋፎች እንዳይገቡ ሲያደርግ የነበረውን መስተጓጎል እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን አለማንሳታቸውን ጠቁመዋል፡፡

እነኚህ የውጪ መገናኛ ብዙሃን መንግስት ላይ ጫና በማሳደር ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚያሰራጩት የሃሰት ዘገባ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃኑ የሀሰት ዘገባዎችን በማሰራጨት ኢትዮጵያ ላይ ጫና በማሳደር የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማስፈጸም ስለመንቀሳቀሳቸውም አንስተዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን በአማራ እና በአፋር ክልሎች እየፈጸመ የሚገኘውን የተለያዩ ግፎች እያዩ ዝምታን መምረጣቸውም በኢትዮጵያ ጉዳይ ለማስፈጸም ያለሙት ድብቅ አጀንዳ ለመኖሩ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡     

ይህ ግን መቼም የማይሳካ የህልም እንጀራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡   

እነኚህ የሀሰት ዘገባ የዕለት ተዕለት ስራቸው እየሆነ የመጡት ሚዲያዎች ሰሞኑንም ኢትዮጵያ ላይ መሰረተ ቢስ ዘገባዎችን ማውጣት መቀጠላቸውን ገልጸዋል፡፡

ሰሞኑን የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎች ሰብል በመሰብሰብ ቤተሰቦቻቸውን እንዲያግዙ ለአንድ ሣምንት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መዝጋቱን የተሳሳተ መልክ ሰጥተው መዘገባቸውን ገልጸዋል፡፡  

እነዚህ መገናኛ ብዙሃን "መንግስት ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት ተማሪዎችን ለጦርነት ማቀጣጠያነት ሊጠቀም ነው" በሚል የዘገቡት ፍጹም ሐሰተኛና የኢትዮጵያዊነትን ባህልን ካለማወቅ የመነጨ መሆኑን ገልጸዋል።

ተማሪዎች ሰብል በመሰብሰብ ቤተሰቦቻቸውንና ወገኖቻቸውን እንዲያግዙ ማድረግ በቀደሙት ጊዜያትም ሲደረግ የቆየ መሆኑን አንስተው በዚህ ዓመትም ተማሪዎች በማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሣተፉ መደረጉ ከኢትዮጵያዊነት ባህል የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁንና አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ይህንን የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህል ለማዳበር የተደረገውን በጎ ተግባር በአሉታዊ መልኩ እየዘገቡት መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ መልኩ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው በመምጣት የአገራቸውን እውነታ እና ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም ለማስረዳት የጀመሩት እንቅስቃሴ የሚያስመሰግን መሆኑን ተናግረዋል።

ዳያስፖራው አገሩ እያሳካች ያለችውን ድል በአካል የሚመለከትበትና አገሩ ላይ ተገኝቶ ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን ማረጋገጫ የሚሰጥበት መሆኑም ሁነቱን ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡  

ለዚህ ስኬት በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ሁሉ የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም