ዝርፊያ እና ማውደምን የዕለት ተግባሩ ያደረገው የህወሓት የሽብር ቡድን ቡርቃ ከተማ ላይ የጭካኔ በትሩን አሳርፏል

70

 ህዳር 25/2014 (ኢዜአ) ዝርፊያን፣ ውድመት እና ጥፋትን የዕለት ተግባሩ ያደረገው አሸባሪው የህወሓት ወራሪ በወገን ጦር ተመቶ ከመውጣቱ በፊት ቡርቃ ከተማ ላይ የጭካኔ በትሩን አሳርፎባታል።

ኢዜአ በቡርቃ ከተማ ባደረገው ምልከታ የሽብር ቡድኑ ወራሪ በርካታ ጥፋቶችን አድርሷል።

በከተማዋ የሚገኙ የግለሰብ ቤቶችን የከባድ መሳሪያ ምሽግ በማድረግ ለጥፋት ዓላማው እንደተጠቀመባቸው ሲወጣ አዝረክርኮ የተዋቸው የጥፋት አሻራዎቹ ምስክሮች ናቸው።

የሽብር ቡድኑ ወራሪ ኢትዮጵያን አፍርሶ ከንቱ ቅዠቱን የመመስረት ህልሙ በጀግኖቹ የቁርጥ ቀን ልጆቿ አኩሪ ተጋድሎ ኮስምኖ ከቡርቃ እና አካባቢዋ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበት ተጠራርጎ ወጥቷል።

በጸያፍ ግብር የተካኑት የሽብር ቡድኑ ወራሪዎች የገቡባት የቡርቃ ከተማ የሕዝብና የመንግስት ተቋማት፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ተዘርፈዋል፣ በቃጠሎ ወድመዋል።

የአካባቢው ምንጮች እንደሚገልጹት የሽብር ቡድኑ ወራሪ ለጥፋት ግብሩ ማርከሻ ይሆንለት ይመስል ያገኘውን ሁሉ ማውደም፣ መዝረፍና ማቃጠል ይቀናዋል።

በቡርቃም የዜጎች መገልገያ የሆኑ ጤና ጣቢያዎች፣ ትውልድ የሚታነጽባቸው ትምህርት ቤቶች፣ ሱቆችና ሌሎችም ተቋማትን በመዝረፍና በማቃጠል አውድሟቸዋል ነው ያሉት።

ከኢትዮጵያ ማህጸን የወጣውን ጡት ነካሽ የሽብር ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማጥፋት አገርና ሕዝብ እፎይታ የሚያገኙበት ወሳኝ ወቅት መድረሱንም ነው የተናገሩት።

በዚህ ወሳኝ የአገር ሉዓላዊነት ማስጠበቂያ ዘመቻ ኢትዮጵያዊያን ከግንባር እስከ ደጀን እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ፍሬ እያፈራ፣ ኢትዮጵያንም ወደ ክብሯ እየመለሳት እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን የወጓት ሁሉ እንደሚወጉ የገለጹልን ምንጫችን የሽብር ቡድኑ እየደረሰበት ያለው ቁሳዊና ሰብዓዊ ሽንፈት ኢትዮጵያ በዘመናት ሂደት የገጠሟትን ፈተናዎች በመሻገር ሉዓላዊነቷን የምታስቀጥል የጽኑ ሕዝቦች ምድር የመሆኗ ምስጢር እንደሆነም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ቀናት የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት የያዘችውን የህልውና ዘመቻ በድል በማጠናቀቅ ድህነትን ወደማሸነፍ የልማት ስራዎቿ ፊቷን እንደምታዞር ያላቸውንም እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም