የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም የበርካቶች ብሩህ ተስፋና የህይወት መሰረት ሆኗል

122

ህዳር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምርጥ የዓለም የቱሪዝም መንደርነት የተመዘገበው የወንጪ ሃይቅ ኢኮ ቱሪዝም የበርካቶች ብሩህ ተስፋና የህይወት መሰረት ሆኗል።

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ዞን ዋና ከተማ ወሊሶ በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የወንጪ ሐይቅ አካባቢው ሰፊ የተፈጥሮ ደን ያለው እንዲሁም ውሃው 360 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋትና ከ6 አስከ 78 ሜትር ጥልቀት አለው።

በምርጥ የዓለም የቱሪዝም መንደርነት የተመዘገበው የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ለአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ በረከቱ ከፍ ብሏል።

በወንጪ ኢኮ ቱሪዝም በጀልባ፣ በፈረስ፣ በማር አምራችነት፣ በአስጎብኚነትና በሌሎችም ዘርፎች በማህበራት የተደራጁ ከ360 በላይ አባላት ይገኛሉ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢኮ-ቱሪዝም ሃላፊው ወዳጀ ተድላ፣ የማር አምራቾች ማህበር ሀብታሙ እጀታ እና የአስጎብኚዎች ማህበር አባል አወቀ አዶኒስ፤ ወንጪ ብሩህ ተስፋና የኑሯቸው መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

የወንጭ ሃይቅ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል ከተደረገ በኋላ በርካቶች የኑሮ መሰረታቸውና የወደፊት ተስፋቸውም አድርገውታል።

የኢኮ ቱሪዝም ተዋናዮች ከወዲሁ የትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማስፋፋት እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም የገቢ ምንጭ በመሆን ኑሯቸውን ለመምራት እንዳስቻላቸውም አስረድተዋል።

ህብረተሰቡ የዛሬን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን የላቀ ተስፋ መጨበጡንም ጠቅሰዋል።

የተፈጥሮ ሀብቱን በአግባቡ በመያዝ የቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ ተፈላጊ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን የሚሰሩ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ይበልጥ እንደሚያድግና እንደሚሰፋ እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ለወንጪ-ደንዲ የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻ ፕሮጀክት በማህበራት ለተደራጁት ብቻ ሳይሆኑ ለአካባቢው ነዋሪዎችም የአሁንና የቀጣይ ተስፋችን ሆኗል ይላሉ።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ሳህሉ ገብረአማኑኤል እና አቶ ጌታቸው ቢረዳ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የተጀመረው የወንጪ ፕሮጀክት ለእኛም ለልጆቻችንም ትልቅ ተስፋ የሰነቀ ሃብት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥነው ስራ ፍለጋ ላይ ከሚገኙት ወጣቶች መካከል ተመስገን ሚልኪያስ እና ማርታ ፊጣ፤ "በወንጪ ሰርተን እንለወጥበታለን ብለን ተስፋ ሰንቀናል" ብለዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም