በህወሓት የሽብር ቡድን የወደሙ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በመጠገን አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ ነው

64

ደብረ ታቦር ፤ ህዳር 25/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ከአሸባሪው የህወሃት ቡድን ወረራ ነፃ በወጡ አካባቢዎች የወደሙ የመሰረተ ልማት አውታሮችንና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ በመገንባትና በመጠገን ስራ ለማስጀመር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

በአማራ ክልል የሰሜን ወሎና የደቡብ ጎንደር ዞን አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማንና ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝተዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍስሃ ደሳለኝ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት ሀገርን ለማፍረስ የወጠነው ሴራ በኢትዮጵያውያን የተባበረ የጀግንነት ተጋድሎ ማክሸፍ ተችሏል።

የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ንጹሃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ የቻለውን ንብረት ዘርፏል፣ ያልቻለውን አውድሟል።

በጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ በጥምረት በደረሰበት ከባድ ምት ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበታል።

አሸባሪው ህወሓት ያወደማቸውን የህዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመገንባትና በመጠገን መልሶ በማቋቋም አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችል  ስራ ተጀምሯል።

ለዚህም የደረሰውን የጉዳት መጠን የሚያጠና እና በቀላሉ ተጠግነው መስራት የሚችሉትን የሚሰራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን ጠቅሰው፤በፍጥነት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ላሊበላ ከተማን ጨምሮ ነፃ በወጡ አካባቢዎች የዕለት ደራሽ ምግብ የማመቻቸት ሥራም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋው ባታብል እንዳሉት ሰሞኑን በተደረገው "ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" በዞኑ አምስት  ወረዳዎችና ሶስት ከተማ አስተዳደሮች ከሽብር ቡድኑ ነፃ ወጥተዋል።

አሸባሪው ቡድን በቆየባቸው ጊዜያት የላሊበላ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያንና ሌሎች የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ የመሠረተ ልማት አውታሮችና የንግድ ተቋማትን አውድሟል።

በሽብር ቡድኑ የወደሙ የመሠረተ ልማት አውታሮችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመጠገንና በማደስ ፈጥኖ ስራ ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ከላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ብርሃኑ ሞላ በሰጡት አስተያየት፤ የሽብር ቡድኑ ለእምነት፣ ለአዛውንት፣ ለህጻንና ለሴቶች እዝነት የሌለው ሕዝብ ጠል ጠላት መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማው በርካታ ጥፋት ከመፈጸሙም ባለፈ መሳሪያና ብር አምጡ እያለ ሲያሰቃያቸው መቆየቱንም አሰታውሰዋል።

አሁን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ተጋድሎ ነፃ በመውጣታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ ለቀጣይ ድል ሰራዊቱን በደጀንነት ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ላሊበላ ከተማን ጨምሮ ሰሞኑን በጋሸና ግንባር ነፃ የወጡ አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ መውደማቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም