ባለፉት አራት ወራት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል

217

ህዳር 25/2014 (ኢዜአ) ባለፉት አራት ወራት ከአንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ያስመዘገቡ 54 ኢንቨስተሮችን መሳብ መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ከሐምሌ 2013 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2014 ዓ.ም ድረስ አንድ ነጥብ 38 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኢንቨስትመንት ለመሳብ አቅዶ ነበር፡፡

ከዚህ ውስጥ አንድ ነጥብ ዜሮ ሰባት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል፡፡

አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ28 በመቶ እድገት ማሳየቱን ያመለከቱት ኮሚሽነሯ፤ ይህም የእቅዱን 78 በመቶ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከተመዘገቡት 54 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ውስጥ 33 የሚሆኑት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ በአገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት የተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አብዛኞቹ ኢንቨስትመንቶች ከቻይና የመጡ መሆናቸውንና ቀሪዎቹ ደግሞ ከተለያዩ አገራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ፤ በተጠቀሱት አራት ወራት ውስጥ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥና ከፓርክ ውጪ ባሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩና ፕሮጀክታቸውን ቀጥለው ምርታቸውን ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

በዚህም የእቅዱን 74 በመቶ ማከናወን እንደተቻለ ገልጸው፤ ከ34ሺ 580 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንና የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች ውስጥ ወደ 24 ሺ የሚጠጉት ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ከተለያዩ አገራት ኢንቨስተሮችና ኤምባሲዎች ጋር ተከታታይ ውይይት መደረጉን ያስታወሱት ኮሚሽነሯ፤ መድረኮቹ ብዙ ልናስተካክላቸው የሚገቡና የብዙ ባለድርሻ አካላትን ጥረት የሚፈልጉ ጉዳዮችን ለመለየት ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግም የኢንቨስተሮችን ችግር በቶሎ ለመቅረፍ የሚረዳ የተቋም ስትራክቸር መፍጠር ችለናል ብለዋል፡፡

ሥራ ላይ ያሉ ኢንቨስተሮች ኮቪድ ባስከተላቸው ችግሮች ውስጥም ሆነ አሁን አገሪቱ ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ብዙ እያገዙንና መንግሥት ላይ ትልቅ እምነት ያላቸው በመሆናቸው ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ኮሚሽር ሌሊሴ ነሜ፤ በቀጣይነትም ኮሚሽኑ እነዚህን ኢንቨስተሮች ባለው አቅም ሁሉ ለማገዝና በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ብትሆንም ጠንካራ ብዙ አቅምና ዕድል ያላት አገር ናት፤ አሁን ያለው ችግር ወደ ከፍታ የምንሻገርበትና የምናልፍበት ዘመን ነው ብለዋል፡፡

ስለሆነም ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ጊዜው አሁን መሆኑን ተገንዝበው ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙና ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!