ከ72 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃ ተያዘ

226

ህዳር 25/2014 (ኢዜአ) ከ72 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው የገቢና የወጪ የኮንትሮባንድ እቃ ባለፈው ሳምንት ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን እንዳስታወቀው ባሳለፍነው ሳምንት በተደረገ ክትትል ከ47 ነጥብ 4 ብር በላይ የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 24 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የወጭ ኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዟል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ ፣ አዳማ እና ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተል 15 ነጥብ 4 ሚሊየን፣12 ሚሊየን እና አምስት ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ነው፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃው የተያዘው የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ በጋራ ባደረጉት ጥረት ሲሆን የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋለው የኮንትሮባንድ እቃ መካከል ወርቅ፣ የተለያዩ አልባሳት፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ቡና፣ መድሀኒት ፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ይገኝበታል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል የጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ማቅረቡን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!