የዞኑ ሴት የመንግስት ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት ከ765 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

83

ነገሌ፣ ህዳር 24/2014/ኢዜአ/ በጉጂ ዞን የሚገኙ ሴት የመንግስት ሰራተኞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ለሶስተኛ ጊዜ በአይነትና በገንዘብ ከ765 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የዞኑ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በዞኑ አዶላ ከተማ የስንቅ ዝግጅት ላይ የተገኙት ሴት የመንግስት ሰራተኞች ሀገር ከደም ከገንዘብና ከቤተሰብ በላይ እንደሆነች ገልጸዋል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ሹገር ጎሎልቻ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ አውደ ግንባር መዝመት በህብረ ብሄራዊ አንድነት ሀገር ለማዳን መነሳሳት ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ከዞኑ ሴት የመንግስት ሰራተኞች ብቻ ለሀገር መከላከያ ሰራዊቱ የሚውል ለሶስተኛ ጊዜ 765 ሺህ 800 ብር ድጋፍ ማድረጋቸውንና  18 ኩንታል ስንቅ ማዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከስንቅ ዝግጅቱ ጎን ለጎንም የዞኑ ሴቶች ለሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ደም በመለገስ ደጀንነታቸውን በተግባር እያሳዩ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

የአዶላ ከተማ ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛ ወይዘሮ ፍቅርተ ሚልኬሶ ሀገር ለማዳን የማይከፍሉት መስዋዕትነት እንደሌለም ገልጸዋል፡፡

ልጅ ወልዶ ለማሳደግ ሀብት አፍርቶ ለመደሰት ሞቶም ለመቀበር ሀገር የሚያስፈልግ በመሆኑ ሀገር ከደም፣ ከገንዘብና ከቤተሰብ በላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

"ለሀገር መከላከያ ሰራዊቱ በመጀመሪያው ዙር ስምንት ሺህ ብር በሁለተኛው ዙር አንድ ሺህ ብር አበርክቻለሁ፤ ደምም ለግሳሸሁ፤ አሁንም ከባልደረቦቼ ጋር ስንቅ እያዘጋጀን ነው" ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ምርት ይልማ በበኩላቸው "ለሀገሬ ያለኝን ፍቅርና ክብር በአይነትና በገንዘብ ድጋፍ ብቻ አይገደብም" ብለዋል፡፡

ሽብርተኛው ህወሓት በሀገርና በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረስው ጥቃት ትልቅ ህመም እንደሆነም ገልጸዋል፡፡  

"ከባልደረቦቼ ጋር በመተባበር 139 ሺህ ብር አውጥተን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ስድስት ኩንታል ስንቅ አዘጋጅተናል" ብለዋል፡፡

በቅርቡ ደም ለግሻለሁ፣ አሁንም ትንሹን ስጦታ ከሶስት ወር በኋላ ደሜን በመለገስ ለመከላከያ ሰራዊቱ ያለኝን ደጀንነት በተግባር አሳያለሁ ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም