ማህበራዊ እሴቶችና የእርቅ ስርዓቶችን ለሀገር ሰላምና ግንባታ ለመጠቀም ዝግጅት እየተደረገ ነው

228

አዳማ፤ ህዳር 24/2014(ኢዜአ) ማህበራዊ እሴቶችና የእርቅ ስርዓቶችን ለሰላምና ሀገር ግንባታ ለመጠቀም የሚያስችል የዝግጅት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቁ።

ሀገር በቀል ማህበራዊ ሀብቶችንና እሴቶችን ለኢትዮጵያ የሰላም ፖሊስ መነሻነትና የስትራቴጂ ማስፈፀሚያነት ለማዋል በሚቻልበት ሂደት ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የአውደ ጥናቱ መድረክ ሲጀመር የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንዳአ ፤  የሀገራችን ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የሚያስተሳስር የጋራ ማንነትና እሴቶች አሉን" ብለዋል።

የመድረኩ ዓላማ ማህበራዊ ሀብቶቻችን ለሰላም እሴትና የሀገር ግንባታ፣ ለአብሮነታችንና ማንነታችን መጠናከር የሚኖራቸውን ፋይዳ በመገምገም ለፖሊስ ግብዓት ለማዋል ነው።

ሚኒስቴሩ  በማህበራዊ ሀብት ልማትና ግንባታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ታዬ፤ ይህም በቀጣይነት ለማዘጋጀት የታሰበውን ሀገር በቀል የሰላም ፖሊስ ግንባታና ስትራቴጅ ወሳኝ የማስፈፀሚያ ግብዓት ለማድረግ እንደሆነ አቶ ታዬ ተናግረዋል።

ህዝቡን በአንድነትና በአብሮነት ያኖሩ የመቻቻልና መተሳሳብ  ማህበራዊ ሀብቶቻችንን በመለየትና በሰነድ በማዘጋጃት ለሀገራዊ ገፅታ ግንባታ ለማዋልም እንዲሁ።

ለሰላማችን፣ ለሀገር ብልፅግና ለአንድነታችን ከውጭ  የሚናስገባው ፖሊስ የለም ያሉት አቶ ታዬ፤ ቱባ ባህላዊ እሴቶቻችን ለሀገርና ሰላም ግንባታ ማዋል አለብን ነው ሲሉም አመልክተዋል።

አሁን በሀገሪቱ የተፈጠሩ ችግሮች የማህበራዊ ሀብቶቻችን በአግባቡ በስራ ላይ ያለማዋልና ከውጭ ከቀጥታ የተቀዱ ፖሊሲዎች ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፖሊስዎቻችን፣ የልማትና እድገታችን እሳቤዎች መነሻው ማህበራዊ እሴቶቻችን መሆን አለባቸው፤  በእውቀትና በእውነት የሀገራችን ብልፅግና እናረጋግጣለን ብለዋል።

ከውጭ የምንፈልገው ነገር የለም ሳይሆን የሀገራችን ማህበራዊ ሀብቶቻችን እንዴት ነው በ"ግሎባላይዜሽን" ውስጥ ዘልቀን ማስገባት የሚንችለው የሚለውን ነው ማየት አለብን ነው ያሉት አቶ ታዬ።

የፍትህ ስርዓቱ ኢትዮጵያዊ መልክ ሊኖረው ይገባል፤ በዚህም ከዳኝነት ስርዓቱ ጎን ለጎን ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን የማደራጀት ስራ መስራት አለበት ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የብሔራዊ መግባባትና ማህበራዊ ሀብት ግንባታ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ሚናስ ፍሰሃ ፤ሀገራችን የተለያየ የማህበራዊ ሀብቶች ቢኖራትም ለፖሊስ መነሻነት ሳትጠቀም ከውጭ  ቀጥታ በመቅዳት ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ስታዳርግ ነበር ብለዋል።

የማህበራዊ እሴቶቻችን በተለይ የብሔር ብሔረሰቦች የእርቅ ስርዓቶች እስከ አሁን በሀገሪቱ የሰላም እሴት ግንባታ ውስጥ እብዛም ሲሰራባቸው አልነበርም ነው ያሉት።

ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ግንባታ ፖሊስ መሰረት የተደረጉት የማህበራዊ የእርቅ ሰላም ስርዓቶች ናቸው ያሉት ዳይሬክተር ጄኔራሉ፤ ባህላዊ እሴቶቻችን ለሰላም፣ልማትና ዕድገት ፖሊስዎቻችን መሰረት የሚሆኑበትን ሂደት ለማመቻቸት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ከውጭ የተቀዱ የሰላም እሴት ግንባታ ፖሊሲዎች  ነበሩን ያሉት አቶ ሚናስ፤ አሁን ግን ኢትዮጵያ የራሷን  ባህልና እሴት ቆጥራ፣ መዝግባና በሰነድ አሰናድታ ለፖሊስ ዝግጅትና የማስፈፀሚያ ስትራቴጅ ግብዓትነት ለመጠቀም ጭምር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም ዘላቂ ሰላም ከመገንባት ባለፈ ለማህበራዊ እሴቶቻችን እውቅና መስጠት፣ ማደራጀትና ተቋማዊ በማድረግ ለልማትና እድገት ለማዋል ነው ብለዋል።

ይህን በተለይ መቻቻል፣ አብሮነትና በይቅርታ ሀገሪቱን ለማሻገር የጎላ ሚና ያላቸውና ለሰላም ግንባታችን ዋናው ምሰሶ መሆን ስለሚገባቸው እንደሆነም አስረድተዋል።

መንግስት በሰላም ሚንስቴር የማህበራዊ እሴቶች ልማት አደረጃጀት በመዘርጋት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በፌዴራል፣ በየክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የባህልና ስፖርት ሴክተሮች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም