በኢኮኖሚው ግንባር ጀግንነትና አገር ወዳድነትን በተግባር መግለፅ ያስፈልጋል

75

ህዳር 24/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር በአሸናፊነት ለመወጣትና በጦርነት የወደመውን መልሶ ለመገንባት በኢኮኖሚ ግንባር ጀግንነትና አገር ወዳድነትን በተግባር መግለፅ ያስፈልጋል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሺሰማ ገብረስላሴ ተናገሩ።

12ኛው ኦል አፍሪካ ሌዘር ሾው እና 7ኛው አፍሪካ ሶርሲንግ የፋሽን ሣምንት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ተከፍቷል።

ከተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት የተውጣጡ 250 የሚሆኑ ኩባንያዎች በዓውደ ርዕዩ ተሳትፈዋል።

በዓውደ ርዕዩ መክፈቻ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሺሰማ ገብረስላሴ አውደ ግንባሩ በጦር ሜዳ ብቻ አለመሆኑን ገልፀዋል።

በአገሪቷ ጦርነቱ ያወደመውን ንብረት ለመገንባትና በአሸናፊነት ለመወጣት በኢኮኖሚው ግንባር ጀግንነትና አገር ወዳድነትን ማስረጽ ያስፈልጋል ብለዋል።

ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር የተሰለፉ አገራት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አፍሪካዊያንና ሠላም ወዳድ የዓለም ሕዝቦች ግፊት እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።

የአገራችንን ነፃነትና ሉዓላዊነት አሳልፈን አንሰጥም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው እንጦጦን ትልቅ ፓርክ እንዳደረግነው ሁሉ በየቦታው ሌሎችም የምንበለጽግባቸው ሃብቶች አሉን ብለዋል።

አፍሪካዊያን በዝግጅቱ ታድመው አዲስ አበባ ስጋት የሌለባት ሠላማዊ ከተማ መሆኗን እያስመሰከሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በቆዳ፣ በጨርቃጨርቅና በሌሎች የአምራች ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ዘርፉ የሚፈለገውን አገራዊ ጥቅም እንዲሰጥ እንሰራለንም ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ተወካይና የአዲስ አበባ ቀጣናዊ ማዕከል ዳይሬክተር አውሬሊያ ካላቦሮ ዓውደ ርዕዩ በሠላማዊዋ እና ውቧ አዲስ አበባ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ዓውደ ርዕዩ ምድረ ቀደምት በሆነችው ኢትዮጵያ ውጤታማና ፍሬያማ የቢዝነስ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑንም አመላክተዋል።

ከቪሌጅ ኢንዱስትሪ የመጡት ዮሴፍ ሲሳይ ደግሞ ድርጅታቸው ከቆዳና ጨርቃጨርቅ ቦርሳና መሰል ምርቶችን  እያመረተ ቢሆንም የጨርቃጨርቅ አቅርቦት ችግር እንደገጠመው ተናግረዋል።

በጨርቃጨርቅ ስራ የተሰማሩት አምሪት ማን በበኩላቸው የተለያዩ አልባሳትን ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልፀው የሰው ሃይሉ በሠዓት ተገድቦ የመስራት አዝማሚያ ሊታረም ይገባል ብለዋል።

አምራቾቹ ዓውደ ርዕዩ ከመሰል ድርጅቶች ጋር ልምድ ለመለዋወጥና ተባብሮ ለመስራት የሚረዳቸው መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ዋና ፀሀፊ ዳንኤል ጌታቸው ዝግጅቱ አምራቾችና ገበያተኞች የንግድ ትስስርና ስምምነት የሚፈጥሩበት መሆኑን ተናግረዋል።

12ኛው ኦል አፍሪካ ሌዘር ሾው እና 7ኛው አፍሪካ ሶርሲንግ የፋሽን ሣምንት እስከ ሕዳር 27 ቀን 2014 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል መካሄዱን ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም