ኢትዮጵያ የገጠማትን የውክልና ጦርነት የሚመክት ትውልድ አካል በመሆናችን ልንደሰት ይገባል

277

አዲስ አበባ፤ ህዳር 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የገጠማትን የውክልና ጦርነት የሚመክት ትውልድ አካል በመሆናችን ልንደሰት ይገባል ሲሉ የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ተናገሩ።

የአገር መከላከያ ሰራዊት ከባዱን ውጊያ እየተዋጋ ነው፣ ሌሎች ደግሞ በየተሰማሩበት ግምባር የተጣለባቸውን ሀላፊነት ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።

ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌን ጨምሮ ሌሎች የመከላከያ ከፍተኛ አዛዦችና ስመጥር ግለሰቦች በጭፍራ ግምባር ለሚገኙ የሰራዊት አባላት የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል።

በዚሁ ጊዜ የሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ፣ የውክልና ጦርነቱን እየመከቱ ያሉ ኢትዮጵያውያን እድለኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ከተሸነፈ መቆየቱን የጠቀሱት ሌተናል ጄኔራሉ፣ አሁን ኢትዮጵያ የገጠማት የውክልና ጦርነት ነው ብለዋል።

ይህም የውስጥ ጠላቶች ለውጪ ሀይሎች ወኪል ሆነው ኢትዮጵያን በይፋ ገጥመዋል ነው ያሉት።

ይህንን ጦርነት እየመከቱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ታሪክ ለዘመናት እየዘከራቸው የሚኖር፣ የቁርጥ ቀን ልጆች ናቸው ብለዋል።

”ይህ ትውልድ የኢትዮጵያን ልዕልናና ከፍታዋን ለማረጋገጥ እድል በማግኘቱ ሊደሰት ይገባል፤ ይህን እድል ማንም አያገኝም” ነው ያሉት።

የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አወል አርባ በበኩላቸው የአፋር ሕዝብ ከመከላከያ ጎን ተሰልፎ የአገር ሉዓላዊነትን እያስከበረ መሆኑን አንስተዋል።

”ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ የሉሲ አገር እንደመሆኗ፣ አፍሪካም አለምም ናት” ያሉት አቶ አወል ኢትዮጵያ ይህንን ክብር ታስቀጥላለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አስተማማኝ ደጀን ያለው በመሆኑ ምንም የማይበግረውና ጠላትን እስከመጨረሻው የሚደመስስ ነው ብለዋል።

የአፋር ሕዝብም ደጀንነቱን በተግባር እያሳየ፣ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር በመሰለፍ ጠላትን እየደመሰሰ መሆኑንም አንስተዋል።

በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ያደረገው ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴም እንዲሁ ሰራዊቱ ከባዱን ግምባር በድል እየተወጣ ይገኛል ብሏል።

ሌላው ኢትዮጵያዊ በያለበት ሁሉ አገር የጣለበትን ሀላፊነት በመወጣት ቀላሉን ግምባር ድል ማድረግ ይኖርበታል ነው ያለው።

”ኢትዮጵያ ለዚህ ሁሉ ችግር የተዳረገችው በድህነቷ በመሆኑ ከድህነት መውጫ መንገዶች ላይ ማተኮር አለብን” ሲልም ጥሪ አቅርቧል።