በኢትዮጵያ ላይ የጥፋት እጃቸውን የዘረጉ ምዕራባውያን አገራት ከእኩይ ተግባራቸው ሊታቀቡ ይገባል

68

አዲስ አበባ፣  ህዳር 24/2014(ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ላይ የጥፋት እጃቸውን የዘረጉ ምዕራባውያን አገራት ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።

ጉባኤው በመግለጫው በኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ ሁሉም ዜጋ በህብረትና በፅናት እንዲቆም ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ጸሀፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ ሁሉም ዜጋ በህብረትና በፅናት እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ላይ እኩይ ዘመቻ የከፈቱና ያልተገቡ ጫናዎችን የሚያሳድሩ ሃገራት፣ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ሚዲያዎች ከአፍራሽ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ገለልተኛ ቢሆንም በአገር ሉዓላዊነት እና የህዝብ አንድነት ላይ የሚቃጡ ድርጊቶችን ይቃወማል ብለዋል።

አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም እና ለሽምግልና ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም በአሸባሪው ህወሃት እምቢተኝነት እንዳልተሳካላቸው ጠቅሰዋል።

የሽብር ቡድኑ አመራሮች ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የእርቅ ሂደቱ ሳይሳካ መቅረቱን አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ የውጭ ጫናዎችን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በይፋ የሚያወግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ ላይ የጥፋት እጃቸውን የዘረጉ ምዕራባውያን አገራትን ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ጉባኤው አሳስቧል፡፡

ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን ጠብቀው፤ የአገራቸውን ህልውና አስከብረው በሰላምና በመከባበር መቀጠል አለባቸው ብሏል ጉባኤው በመግለጫው።

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ጥቅም በመቆም አገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።

የጉባኤው መግለጫ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ለአለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለኤምባሲዎች እና ለተለያዩ አለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት እና ድርጅቶች በተለያዩ ቋንቋዎች የሚላክ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም