ብሔር ብሔረሰቦች ለህልውና ዘመቻው በአንድነት በመቆም የጀመሩትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

62

ባህር ዳር፤ ህዳር 24/2014(ኢዜአ) በውስጥ ባንዳዎች እና በውጭ ጠላቶች በሀገር ላይ የተደቀነው የህልውና አደጋ በድል አድራጊነት ለመሻገር ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት የጀመሩትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ።

"ወንድማማችነት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ ዘንድሮ ለ16ኛ ጊዜ የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በመረሃ ግብሩ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንዳሉት፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከውስጥ ባንዳዎችና ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተባብሮ እየሰራ ነው።

በህዝብ የተመረጠን መንግስት በእብሪት ለማፍረስ የተነሳውን ይህን ቡድን ከነ ክፉ አስተሳሰቡ ለማስወገድ ብሔር ብሔረሰቦች ለህልውና ዘመቻው በአንድነት የጀመሩትን አስተዋፅኦ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የባለ ብዙ ታሪክ ባለቤት መሆኗን ገልጸው፤ ለዚሀም  የአድዋን አኩሪ  ድልን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

"የአድዋ ድል ሚስጥሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተሳትፈው ወራሪውን ጠላት መደምሰስ መቻላቸው ነው" ያሉት አፈ ጉባኤዋ፤ ድሉም ዛሬ ድረስ ለመላው የጥቁር ህዝብ ምሳሌ መሆኑን አውስተዋል።

"የአሁኑ ትውልድም እህትና ወንድማማችነትን በማጠናከር የህልውና ዘመቻውን በላቀ ድል አድራጊነት በማሸነፍ የራሱን አኩሪ ታሪክ መድገም ይኖርበታል" ብለዋል።

ዘንድሮ ለ16ኛ ጊዜ የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ዛሬ የተደረገው የደም ልገሳም የህልውና ዘመቻው አንዱ አካል መሆኑን ነው የጠቆሙት።


የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ በበኩላቸው፤  "ሠራዊቱ በአሁኑ ወቅት እያስመዘገበ ያለው ድል በደጀንነት የተሰለፈውን ህዝብ ሞራል ከፍ አድርጎታል" ነው ያሉት።


"በየግንባሩ እየተሰማ ያለው የድል ዜና ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ሁላችንም ደም በመለገስና ስንቅ በማዘጋጀት የደጀንነት ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል" ብለዋል።


የሀገርን ክብር ጠብቆ ለማቆየት ወጣቱ የመከላከያንና ልዩ ሃይሉን መቀላቀል እንዳለበት የጠቆሙት ሃላፊዋ፤ መዝመት የማይችለው አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች በንቃት እንዲጠበቅም አሳስበዋል።


ከዕለቱ ደም ለጋሾች መካከል አቶ አንዳርጋቸው ጎፋ፤ በሰጡት አስተያየት፤ "አሸባሪው ህወሓት በመሰሪ ባህሪው ሊያፈርሳት የነበረችው ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ መስዋትነት ነፃነቷ ተከብሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

ሀገርን በመታደግ የቀድሞ ክብሯን ለመመለስ በግንባር ለሚፋለሙ የወገን ጥምር ጦር አባላት የቅርብ ደጀንነታቸውን ለማሳየት ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል።


"ሁላችንም በምንችለው አቅም ሁሉ ለመከላከያ ሠራዊቱ ሁለንተናዊ ድጋፋችንን ማስቀጠል ይገባናል" ብለዋል።

በደም ልገሳ መርሃ ግብር ከፍተኛ አመራሮች ፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ሠራተኞችና አካል ጉዳተኞች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም