"ለሽብር ቡድኑ የተሰለፋችሁ ሁሉ እጃችሁን በሠላም ስጡ፣ ሕይወታችሁንም አትርፉ" - የሽብር ቡድኑ ታጣቂ የ17 ዓመት ታዳጊ

79

ህዳር 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ለሽብር ቡድኑ የተሰለፋችሁ ሁሉ እጃችሁን በሠላም ስጡ፣ ሕይወታችሁንም አትርፉ" ሲል የሽብር ቡድኑ ታጣቂ የ17 ዓመት ታዳጊ አማኑኤል መንግስቱ አስገነዘበ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፣ ጠላት እየተበተነ መሆኑንና የህወሓት የሽብር ቡድንን የተቀላቀለና ጥፋት እያደረሰ ያለ ማንኛውም ታጣቂ በአስቸካይ እጅ እንዲሰጥ ማሳሰባቸው ይታወቃል።

"ያለ አባት ከምታሳድገኝ እናቴ ነጥቀው በመውሰድ በጦርነት ውስጥ ማግደውኛል" ያለው እጁን በሠላም የሰጠው ታዳጊ አማኑኤል መንግስቱ፤ ለሽብር ቡድኑ የተሰለፉ ሁሉ ህይወታቸውን እንዲያድኑ መክሯል።

አማኑኤል መንግስቱ ውልደትና እድገቱ በማይጨው ከተማ ቀበሌ ዜሮ ሁለት እንደሆነ ይናገራል፤ የ8ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበረም ገልጿል።

ታዳጊ አማኑኤል "ለሽብር ቡድኑ የተሰለፋችሁ ሁሉ እጃችሁን በሠላም ስጡ፣ ሕይወታችሁን አትርፉ" ብሏል።

በመልካም ሁኔታ እና ጤንነት ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ እጁን ከሰጠ ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሚበሉትንና የሚጠጡትን በማካፈል እንክብካቤ እያደረጉለት እንደሚገኝም ተናግሯል።

ታዳጊው በሽብርተኛው ህወሓት መሪዎች ያለ አባት ካሳደገችው እናቱ በግዳጅ ተነጥቆ በጭፍራ ግንባር ተሰልፎ እንዲዋጋ ግዳጅ እንደተሰጠው ተናግሯል።

ነገር ግን ስለ ጦርነቱና ስለ አካባቢው ምንነት እንኳን በቅጡ መረዳት አለመቻሉንና እጁን በሠላም ለአገር መከላከያ ሠራዊት በመስጠት ሕይወቱን በተዓምር ማትረፉን ነው የገለጸው።

የሽብር ቡድኑ እንደሚያሰራጨው ጥላቻና ስም ማጥፋት ሳይሆን ለእሱና ለሌሎችም በመከላከያ ሠራዊቱ ጨዋነት የተሞላበት እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሆነም ገልጿል።

እጁን በሠላም በመስጠት ሕይወቱን ማትረፍ በመቻሉ ደስተኛ እንደሆነም ነው ታዳጊው የተናገረው።በወገን ጦር የሚሰነዘርበትን ከባድ ምት መቋቋም የተሳነው የሽብር ቡድኑ ህወሓት ወራሪ ሀይል በየዓውደ ግንባሩ እየተደመሰሰ፣ እየተማረከ እና እጁን እየሰጠ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም