የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋነኛ ተጠቃሚ የሆነው ኅብረተሰብ ሕጉን አክብሮ ሊንቀሳቀስ ይገባል

67

አዲስ አበባ ህዳር 24/2014 (ኢዜአ) በትግበራ ላይ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኅብረተሰቡ የተረጋጋና ሠላማዊ ሕይወት እንዲመራ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን የታሪክና የሕግ መምህሩ ዶክተር አልማው ክፍሌ ገለጹ፡፡

ዶክተር አልማው ክፍሌ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የሕግ መምህር እንዲሁም የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ዋና ፀሃፊ ናቸው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶክተር አልማው ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለኅብረተሰቡ ሠላማዊ ሕይወት መቀጠል ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋነኛው ተጠቃሚ ኅብረተሰቡ በመሆኑ ሕጉን አክብሮ ሊንቀሳቀስ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሸባሪው ህወሓት የሕዝብና የአገር ሉዓላዊነትና ደህንነት ላይ አደጋ የሚጥል ወረራ በመፈጸሙ መታወጁን አስታውሰዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱና አገር የማፍረስ ሙከራ በማድረግ ላይ መሆኑን በመጥቀስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይህን ለማክሸፍ ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

እነዚህንና መሰል ድርጊቶችን በመደበኛ ሕግ በማስተናገድ ሠላም ማምጣት ስለማይችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል።

አዋጁ ለአሸባሪው ህወሓትና ለተላላኪው ሸኔ የመጨረሻ ድምዳሜ መስጠት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡

የሚስተዋለውን ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመቆጣጠርና ሰርጎ ገቦችን ተከታትሎ ለመያዝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣት አስፈላጊ እንደነበረም ነው ዶክተር አልማው ያስረዱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም