ፈተናውን ለማለፍ የቀደመ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህላችንን ልናጎለብት ይገባል

101

ደብረ ብርሀን፣ ህዳር 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) "እንደ ሃገር የገጠመንን ፈተና በአሸናፊነት ለማለፍ የቀደመ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህላችንን ይበልጥ ማጎልበት ይገባናል" ሲሉ የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ገለጹ።

ኮሚሽኑ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በፈጸመው ወረራ  ለተፈናቀሉና በህልውና ዘመቻው ጉዳት ለደረሰባቸው 35 ሚሊየን ብር የሚገመቱ ምግብ ነክና ሌሎች ቁሳቁሶችን አበርክቷል።

የድጋፍ ርክክቡ በደብረ ብርሃን ከተማ በተካሄደበት ወቅት የጉሙሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ እንዳሉት፤ አሸባሪዎቹ ህውሃትና ሸኔ  አገር ለማፍረስ የያዙት ዓላማ በወገን የፀጥታ ሃይሎች እየከሸፈ ይገኛል።

"አሸባሪዎቹ የደቀኑትን አደጋ ለማለፍ የቀደመ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህላችንን ልናጎለብት ይገባል" ብለዋል።

በተለይም በጦርነቱ የተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችን መደገፍ የሁሉም ድርሻ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ኮሚሽኑ በአሸባሪ ቡድኑ ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው 35 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አድርጓል" ብለዋል።

የኮሚሽኑ ድጋፍ ቀጣይነት እንደሚኖረውም አረጋግጠዋል።

ከዚህ ሌላ ኮሚሽኑ የሀገሪቱን የንግድ ሚዛን ለመጠበቅ  ህገ ወጥ ንግድና ያልተፈቀዱ የንግድ እቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ እዳይገቡ በመከላከል የህልውና ዘመቻውን እየደገፈ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ቤተልሄም ላቀው በበኩላቸው፤ በአሸባሪው ቡድን ተንኳሽነት ሳንፈልገው ተገደን ለገባንበት ጦርነት በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ አንድነትን ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል።

በቀጣይ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት እንደ ጉሙሩክ ኮሚሽን ሁሉ ሁሉም እንዲረባረብ መልዕክት አስተላልፈዋል።

''ለህልውና ዘመቻውና ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመደገፍ አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ህዝባዊ ንቅናቄ የሚደነቅ ነው'' ያሉት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሎጅስቲክ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሲሳይ ወልደአማኑኤል ናቸው።

ጉሙሩክ ኮሚሽን ለወገን እያደረገ ላለው ድጋፍ  አመስግነው፤ በቀጣይ ዜጎችን ለማቋቋም እገዛው  መጠናከር እንዳለበትም አመልክተዋል።

በአሸባሪው የህሃት ቡድን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ጊዜያዊ መጠለያና በዘመድ ቤት ተጠግተው ለሚገኙ 443 ሺህ ወገኖች በተቻለ መጠን ድጋፍ እንዲደርሳቸው እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም