በአሪ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል 'ድሽታ ግና' የዘማች ቤተሰቦች ይጠየቃሉ

110

ህዳር 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዘንድሮው የአሪ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ 'ድሽታ ግና' በዓል የዘማች ቤተሰቦች ይጠየቃሉ፣ የደም ልገሳ በማድረግ ለአገር መከላከያ ሠራዊት አጋርነት ይገለጻል።

በመጪው ሣምንት ታህሳስ 1 ቀን 2014 ዓ.ም የሚከበረውን የአሪ ብሄረሰብ የድሽታ ግና የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ሲምፖዚየም፣ ውይይትና ለመከላከያ ሠራዊት የደም ልገሳ መርሃ ግብር ተከናውኗል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሊጂ  መምህር ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶ፣ የብሄረሰቡ ተወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሃ ግብሩ ታድመዋል።

ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶ ድሽታ ግና የሚሰኘው የአሪ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል እርስ በርስ የመረዳዳት፣ የአዲስ ብስራትና የተስፋ መገለጫ በዓል መሆኑን አስረድተዋል።

በየዓመቱ ታህሳስ 1 ቀን የሚውለው የድሽታ ግና በዓል ዘንድሮ በጂንካ ከተማ ይከበራል ብለዋል።

የዘመን መለወጫው በዓል የአገር መከላከያ ሠራዊቱን የተቀላቀሉ ዘማቾች ቤተሰቦችን በመጠየቅ እንዲሁም ለመከላከያ ሠራዊት አጋርነትን ለመግለጽ የደም ልገሳ በማድረግ እንደሚከበር ተገልጿል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም