ክፍለ ከተማው ለሰራዊቱ 16 ሚሊየን ብር ድግፍ አደረገ

166

ደብረ ብርሀን/ ኢዜአ /ህዳር 23/2014 በአዲስ አበባ ከተማ የቂርቆስ ከፍለ ከተማ አስተዳደር ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና ምግብ ነክ ድጋፍ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት አደረገ።
ኢትዮጵያ ጠል በሆኑ የውጭ ኃይሎችና በውስጥ ባንዳዎች የተከፈተብን ሀገር የማፍረስ ዘመቻ በመመከት ዳግም የአደዋን ድል ለማስመዝገብ ሁሉን አቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።

የቂርቆስ ከፍለ ከተማ አስተዳደር ለሀገር  መከላከያ ሠራዊት ያደረገውን ምግብና ምግብ  ነክ ድጋፉን  በጣርማበር ወረዳ በመገኘት ለሠራዊቱ አስረክቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በርክክብ ሥነስርዓቱ ላይ እንደገለጹት አሁን ላይ የተገኘው ወታደራዊ ድል ሁሉንም አኩርቷል።

የተገኘው ድል በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ ተቀጣሪ ባንዳዎችን ቅስም ከመስበሩም በላይ የአባቶቻችን የድልና አየሸናፊነት ታሪክ የተደገመበት ወቅት መሆኑንም ገልፀዋል።

መከላከያ ሰራዊት ለሀገርና ለህዝብ ሕልውና፣ ሉዓላዊነትና ክብር እየከፈለ ያለው መስዋትነት ታሪክ የሚዘክረው መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሰራዊቱ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘመኑ ታደሰ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር መዝመት ሁሉንም አመራርና ሰራተኛ ወኔ የቀሰቀሰ ነው።

ከጠቅላይ ሚስትሩ መዝመት ጋር ተያይዞ የመጣውን ሀገራዊ ድል ለማስቀጠል በተሰማራንበት የስራ መስኮች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

የክፍለ ከተማው አስተዳደር ከመከላከያ ሰራዊት ጋር የምሳ ፕሮግራም ለማድረግ ዛሬ በጣርማበር መገኘቱን ገልፀው፤ ከ16 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

”እኛ በጦር ሜዳ ተሰልፈን ለምናስመዘግበው ድል የህብረተሰቡ ድጋፍ ከፍተኛ ሚና አለው” ያሉት ደግሞ ድጋፍ የተረከቡት ሌተናል ኮለኔል ለችሳ መገርሳ ናቸው።

ኢትዮጵያን ለማተራመስ ጦር የመዘዙትን የአሸባሪው ህውሓት ጁንታና የሸኔ አባላት የእጃቸውን እያገኙ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ በኢኮኖሚና በሞራል ከሚያደርግልን ድጋፍ ባሻገር የጁንታው ግብር አበሮችን ለይቶ ለህግ እንዲቀርቡ እያደርገ ያውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

መላው ኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችን ቆማችሁ ለምታደርጉልን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬ የድረሳችሁ ብለዋል።