የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለተፈናቃዮች 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ

161

ባህርዳር ህዳር 23/2014 የኢትዮጵያ አትሌክስ ፌደሬሽን በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

 የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በርክክብ ሥነስርዓት ላይ እንዳሉት አሸባሪው ህውሓት የአማራና አፋር ክልሎችን በመውረር በንጹሃን ዜጎች ላይ ግፍ ፈጽሟል።

በርካታ ንጹሃን ዜጎችን በመግደል፣ ኃብት ንብረታቸውን በመዝረፍና በማውደም ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ በማድረግ ለመከራና ለስቃይ መዳረጉንም ገልጸዋል።

ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለው የሚገኙ ወገኖቻችን ላይ የደርሰው ችግር የእናንተ ብቻ ሳይሆን የእኛም በመሆኑ በመንፈስም ሆነ በአካል ከናንተው ጋር ነን ብለዋል።

ሌሎች የስፖርት ፌደሬሽኖችም በቅርቡ ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ወደፊትም ክልሉ የገጠመውን ችግር ለማስወገድ አብረን በመበረታት የሚያልፈውን ችግር በማያልፍ ፅናት በጋራ ለመወጣት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የፌደሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ በበኩላቸው ፌደሬሽኑ ያመጣው ድጋፍ  1000 ፍራሾች፣ 836 ኩንታል ዱቄትና ቅንጨ እንዲሁም 700 ከረጢት ባለ 25 ኪሎ ግራም ማኮረኒ መሆኑን አስረድተዋል።

ድጋፉ በባህርዳር ከተማ ከሚገኙ ባለሃብቶች የተገዛ ሲሆን፤ ይህም የአካባቢውን ግብይት የሚያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል።

 የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ምክትል ኮሚሽነር እታገኘሁ አደመ በበኩላቸው አሸባሪው ቡድን በክልሉ ላይ በፈጸመው ወረራ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎችን በመደገፍ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ያደረገው ርብርብ የሚበረታታ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር ሲታይ ተጨማሪ ጥረት የሚጠይቅ እንደሆነም ተናግረዋለ።

ፌደሬሽኑ ያደረገው ድጋፍ የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግር ለማቃለል አጋዥ እንደሚሆን ገልጸው፤ በቀጣይም ሌሎች አካላት ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የተደረገውን ድጋፍ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በፍትሃዊነት እንደሚደርሳቸው አረጋግጠዋል።

በአማራ ክልል በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ከመኖሪያ ቀየው ተፈናቅሎ በችግር ውስጥ እንደሚገኝ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።