የጤና ሚኒስቴር በስምንት ክልሎች ዘመናዊ ላቦራቶሪዎችን ሊያስገነባ ነው

202

ህዳር 23/2014 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴር በስምንት ክልሎች በ150 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ዘመናዊ የሕክምና ላቦራቶሪዎችን ሊያስገነባ ነው።
ላቦራቶሪዎቹ ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍና ብድር የሚገነቡ ሲሆን ግንባታው በአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ይከናወናል ተብሏል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በ6 ክልሎች የሚገነቡትን የመጀመሪያዎቹን 9 ላቦራቶሪዎች ግንባታ ለማከናወን ከ7 አገር በቀል ሥራ ተቋራጮች ጋር ዛሬ የውል ሥምምነት ተፈራርመዋል።

ዶክተር ሊያ ታደሰ ጉዳዩን አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ የሚገነቡት ላቦራቶሪዎች በውጭ አገራት ብቻ ይሰጡ የነበሩ ምርመራዎችን ለመሥጠት ያስችላሉ ብለዋል።

የላቦራቶሪዎቹ ግንባታ የአገሪቱን የጤና አሰጣጥ ለማሻሻል የተያዘውን የስትራቴጂክ ትኩረት አቅጣጫ ለማሳካት ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለውም ተናግረዋል።

ለአምስት ዓመት በሚቆየው በዚሁ ፕሮጀክት በፌዴራልና በክልሎች በርካታ ላቦራቶሪዎችና ተያያዥ መሰረተ ልማቶች እንደሚገነቡ ገልጸዋል።

የመጀመሪያዎቹ ላቦራቶሪዎች የሚገነቡት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣  በሶማሌ፣ በአፋርና በጋምቤላ ክልሎች መሆኑን ጠቅሰው ግንባታቸውም በሰኔ 2015 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

የላቦራቶሪዎቹ ግንባታ በ571 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚከናወን ጠቁመው የገንዘብ ድጋፍና ብድር ፕሮጀክቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁንም ተናግረዋል።

የላቦራቶሪዎቹ መገንባት ከጎረቤት አገራት ጋር በመተባበርና በመቀናጀት በተለይ በመግቢያና መውጫ በሮች አካባቢ የሚሰሩ የወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎችን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋልም ብለዋል።

ግንባታውን ለማከናወን ውል የገቡ የሥራ ተቋራጮች ሥራውን በጥራት እንዲያከናውኑና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲያጠናቅቁም ጥሪ አቅርበዋል።