በጭሮ ከተማ 1ሚሊየን 200ሺህ ብር በሆነ ወጪ የተገነቡ የመስሪያ ሼዶችን ለተጠቃሚዎች ተላለፈ

169

ጭሮ፤ህዳር 23/2014 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ቢሮ ቤዛ ለወገን ከተሰኘ ማህበር ጋር በመሆን በጭሮ ከተማ 1ሚሊየን 200ሺህ ብር በሆነ ወጪ ያስገነባቸው የመስሪያ ሼዶችን ለተጠቃሚዎች አስተለላለፈ።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ አዱኛ አህመድ  መስሪያ ቦታዎቹ በተላለፉበት ወቅት እንዳሉት፤  ቢሮው የህግ የበላይነትን ከማስከበርና ፍትህን ከማስፈን በተጓኝ   ችግረኛ ወገኖችን ለመደገፍ ጥረት እያደረገ ነው።

“እኛ እያለን ወገናችን አይቸገርም፣ ዓላማ ይዞ የተነሳው የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ በጭሮ ከተማ ቤዛ ለወገን ከተሰኘ ማህበር ጋር በመሆን ለንግድ የሚሆን  የመስሪያ ሼዶችን አስገንብቶ ለተጠቃሚዎች አስረክቧል” ብለዋል፡፡

የጭሮ ከተማ አስተዳደር ለንግድ ምቹ የሆነ የግንባታ ቦታ በመስጠት፣ በከተማው የሚገኙ የህግና ፍትህ አካላት ደግሞ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ለስራው መሳካት ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

የፍትህ አካላት ህግን ከማስከበር ባሻገር ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ችግር ለማቃለል አዋጪ  የንግድ ተቋማት በቀጣይ በከተማው እንደሚያስገነቡም ተመልክቷል፡፡

የቢሮው   የስርዓተ ጾታ ፣ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክተር ወይዘሮ ሚሚ ሀብተ ወልድ በበኩላቸው ፤በጭሮ ከተማ ከሚደገፉ 21 ሰዎች መካከል 15 ህጻናትና ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው የሚገኙ ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለሼዶቹ ግንባታ 1ሚሊዮን 200ሺህ ብር ወጪ መደረጉንና ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች በዕጣ እንዲተላለፉ ተደርጓል።

የጭሮ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድ ኡመር፤ ቢሮው  በከተማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና በህመም ምክንያት ለችግር ከተጋለጡ  ወገኖች ጎን በመቆም ያከናወነው የበጎ አድራጎት ስራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም  ለሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች ምሳሌ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

የመስሪያ ሼድ ከተሰጣቸው መካከል ወይዘሮ አዲስ በለጠ ፤ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፤  ወደ ፊት ህይወታቸውን ለመለወጥ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸውም ተናግረዋል፡፡

ይህን እድል ተጠቅመው ጠንክረው በመስራት ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን  እንደሚጥሩ ነው ወይዘሮ አዲስ የገለጹት፡፡

አቶ ሀሮን አብደላ በበኩላቸው፤ ቢሮው ቀደም ሲል የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረገላቸው አስታውሰው፤  አሁን በተሰጣቸው የመስሪያ ቦታ ጠንክረው በመስራት እራሳቸውን ለመለወጥ መነሳሳታቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግስት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን እየለየ እየደረገ ባለው ድጋፍ መደሰታቸውንም ገልጸዋል።