የአየርላንድ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ያለውን የተሳሳተ አቋም እንዲያስተካክል የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ጥረት እየተደረገ ነው

136

አዲስ አበባ ህዳር 23/2014(ኢዜአ) የአየርላንድ መንግስት በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ያለውን የተሳሳተ አቋም እንዲያስተካክል የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው በአየርላንድ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።

ኢትዮጵያና አየርላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1994 መጀመራቸውን መረጃዎች ያመዐላክታሉ፡፡

በዚህም  ሁለቱ አገራት በልማት መስኮችና ጠንካራ ሊባል የሚችል ግንኙነት ፈጥረዋል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት ግን የአየርላንድ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ ዙሪያ የያዘው አቋም ለአንድ ወገን ያደላ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

አየርላንድ የኢትዮጵያን እውነት እንድትገነዘብ ለማድረግ ‘ቮይስ ፎር ኢትዮጵያ አየርላንድ’ የተሰኘ ግብረ ሃይል በታህሳስ ወር 2013 ዓ.ም ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።

በአየርላንድ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለኢዜአ እንደተናገሩት አየርላንድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባዎች በተደጋጋሚ ጊዜ እንዲጠሩ በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ ግፊት ስታደርግ ቆይታለች።

ይሄ የአየርላንድ አካሄድ የዳያስፖራውን ማህበረሰብ ያላስደስተና ተቀባይነት የሌለው ድርጊት እንደሆነ አመልክተዋል።

ሁለቱ አገራት ከ30 ዓመት በላይ ካስቆጠረው መልካም ግንኙነታቸው አንጻር አየርላንድ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን አቋም እንድታስተካክል ግፊት ማድረግ መጀመሩን ነው ዳያስፖራዎቹ የሚገልጹት።

የአየርላንድ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የያዘውን አድሏዊ አቋም እንዲያስተካክል ለአገሪቷ ፓርላማ አባላት በተደጋጋሚ ጊዜ ደብዳቤ በመጻፍና የማነጋገር ስራ በዳያስፖራው እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም ዳያስፖራው በየሚኖርበት አካባቢ የሚገኙ ተወካዮቹን በየጊዜው በማነጋገር የኢትዮጵያን እውነት እንዲያውቁት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና የአየርላንድን የፖለቲካ ሁኔታ በውል የሚረዱ የአየርላንድ ዜጎች ሚኒስትሮችን አግኘተው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ እንዲነጋገሩ መደረጉንም አመልክተዋል።

በዚህም የአየርላንድ መንግስትና ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ለመረዳትና ነገሮችን ቆም ብሎ ለማየት ፍላጎት ማሳየታቸውን ነው ዳያስፖራዎቹ የገለጹት።

የአየርላንድ መገናኛ ብዙሃንም በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚያወጧቸውን ለአንድ ወገን ያደሉ ዘገባዎች ለውጥ እየታየባቸው መሆኑንና በተለይም አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ላይ የፈጸመውን ወረራና ያደረሰውን ጉዳት መናገር መጀመራቸውን አመልክተዋል።

ጅማሬው ጥሩ ቢሆንም የአየርላንድ መንግስት ኢትዮጵያን በተመለከተ ትክክለኛ አቋም እስኪይዝ የተቀናጀ ስራ እንደሚጠይቅ ነው ዳያስፖራዎቹ የተናገሩት።

በሰላማዊ ሰልፍ መቃወምን ጨምሮ በቀጣይ ዘላቂነት ያለው የዲፕሎማሲ ስራዎችን በማከናወን የአየርላንድ መንግስት በኩል ለውጥ እንደሚመጣ አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በአየርላንድ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለታላቁ የኢትጵያ ሕዳሴ ግድብ ጨምሮ ለሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች፣የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳትና ለማቋቋምና ለአገራቸው አስፈላጊውን ድጋፍ የማድረግ ተግባራቸውን በተጠናከረ መልኩ እንዲሚቀጥሉም ዳያስፖራዎቹ አስታውቀዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሕዳር 15 ቀን 2014 ዓ.ም ከተልዕኳቸው ውጭ ሲንቀሳቀሱ ያገኛቸውን አራት የአየርላንድ ዲፕሎማቶች በሳምንት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ መወሰኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም