በዲፕሎማሲው መስክ የተለያዩ አገሮች ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን በተግባር እያሳዩ ነው

79

አዲስ አበባ፣ህዳር 23/2014 (ኢዜአ) በዲፕሎማሲው መስክ ያልተገባ ጫና የሚያደርጉ አገሮች ቢኖሩም የተለያዩ አገሮች ደግሞ ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን በተግባር እያሳዩ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልገሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ፤ በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና የሚያደርጉ አገሮች ቢኖሩም የኢትዮጵያን እውነታ የተረዱ አገሮች ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን በተግባር እያሳዩ ነው ብለዋል።

አንዳንድ አገሮች ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዡ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

ቻይና ከአፍሪካ አገራት ጋር አዲስ የንግድ ትስስር ለመፍጠር የጀመረችው እንቅስቃሴም የቻይና አፍሪካን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ላይ ከጉዳዩ በተጨማሪ ዲፕሎማሲያዊ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደምትሆን ጠቅሰው የሁለቱ አገሮች ሁለንተናዊ ትብብርም ወደ ላቀ ደረጃ ይሸጋገራል ብለዋል።  

በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን ያልተገባ የውጭ ጫና በመቃወም የተጀመረው "የበቃ- No more" ዘመቻ በርካቶች ተቀላቅለውታልም ነው ያሉት።

በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት በመምጣት በተለያዩ በዓላት ላይ እንዲታደሙ መንግስት ጥሪ ማቅረቡንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት ከከፈተው ጦርነት ጋር በተገናኘ በመንግሥት ላይ ሲሰነዘሩ የነበሩ አሉባልታዎች ትክክል አለመሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ባቀረቡት ሪፖርት አረጋግጠዋል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የአንዳንድ አገራት ኢምባሲዎች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ትከክል ያልሆኑ መግለጫዎችን ማውጣታቸውን መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

እውነታው ግን እነርሱ እንደሚሉት ሳይሆን አዲስ አበባ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ከተማ ሆና ቀጥላለች ብለዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም