በምሥራቅና በምዕራብ የተገኘው ድል በመሐል ሀገር እንደሚደገም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ

59

ህዳር 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምሥራቅና በምዕራብ የተገኘው ድል በመሐል ሀገር እንደሚደገም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄንን የተናገሩት በሦስተኛው ቁልፍ ግንባር ተገኝተው ከሠራዊቱ ጋር በመከሩበት ጊዜ ነው።

ከሰሞኑ በሚሠሩ ኦፕሬሽኖች በወራሪው አሸባሪ የተያዙ ተጨማሪ ከተሞች ነጻ እንደሚወጡ የገለጹ ሲሆን ለወረራ የገባው አሸባሪ ምንም ነገር ይዞ እንዳይወጣ ሕዝቡ ተደራጅቶ ማስቀረት እንዳለበት ጥሪ አድርገዋል።

ጠላት ፈርሷል፤ ተበትኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ አሁን ጠላት ያለው አማራጭ የሰረቀውን አስረክቦ እጁን መስጠት ነው ብለዋል።

የሰረቀውን አስረክቦ እጁን ከሰጠ ምርኮኞችን ተንከባክቦ መያዝ የጀግና ባህላችን ነው ብለዋል።

ከአሸባሪው ሕወሓት ነጻ በወጡ አካባቢዎች በአስቸኳይ መስተዳድሩን በቶሎ መልሶ ማቋቋም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነዋል፤ ወታደሩ በከፍተኛ ሞራል ላይ ነው ሲሉም የወገን ኃይል ያለበትን ሁኔታ ገልጸዋል።

ሕዝቡ እስካሁን ላደረገው ተሳትፎ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን አንድነታችን የተጠበቀ ይሁን፤ የአሉባልታ ወሬ ወጀብ አይውሰደን፤ አንድ ሆነን የማትደፈር ሀገር ለልጆቻችን እናስረክብ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም